ሪፖርት | ኢትዮጵያ መድን ከ12 ጨዋታዎች በኋላ ከድል ጋር ታርቋል

ኢትዮጵያ መድን ከመመራት ተነስቶ በአብዱልከሪም መሐመድ ሁለት ግቦች መቻልን 2ለ1 መርታት ችሏል።

ተጠባቂ በነበረው መርሐግብር መቻል እና ኢትዮጵያ መድን ተገናኝተው መቻሎች በ20ኛው ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር 0-0 ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ በቅጣት ላይ በሚገኘው ዳዊት ማሞ ምትክ ዮዳሄ ዳዊትን ሲያስገቡ ኢትዮጵያ መድኖች በአንጻሩ ከሲዳማ ቡና ጋር ያለ ግብ ከተለያዩበት አሰላለፍ ባደረጉት የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በርናንድ ኦቼንግ እና ሀይደር ሸረፋ በሰዒድ ሀሰን እና አሚር ሙደሲር ተተክተው በቋሚነት ተካተዋል።


ምሽት 1 ሰዓት ሲል በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ መሪነት በተጀመረው ጨዋታ እጅግ ፈጣን አጀማመር ያደረጉት መቻሎች በሴኮንዶች ውስጥ ጎል አስቆጥረዋል። ዮዳሄ ዳዊት ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ምንይሉ ወንድሙ በግንባሩ ከገጨው በኋላ ሽመልስ በቀለ ኳሱን በተረጋጋ አጨራረስ መረቡ ላይ አሳርፎታል። መቻሎች 4ኛው ደቂቃ ላይም ተጨማሪ የግብ ዕድል ፈጥረው ምንይሉ ወንድሙ ኳሱን ሳያገኘው ቀርቶ አባክኖታል።

የአቻነት ግብ ፍለጋ መታተራቸውን የቀጠሉት ኢትዮጵያ መድኖች 10ኛው ደቂቃ ላይ ተሳክቶላቸዋል። የመቻሉ አቤል ነጋሽ ከሳጥን አጠገብ ያደረገውን ሙከራ ግብ ጠባቂው ተክለማርያም ሻንቆ ከመለሰው በኋላ በመልሶ ማጥቃት ወስደውት ጄሮም ፊሊፕ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ወደ ውስጥ የቀነሰውን ኳስ ግብ ጠባቂው አልዌንዚ ናፊያን ሲመልሰው የተመለሰውን ኳስ ያገኘው የቀኝ መስመር ተከላካዩ አብዱልከሪም መሐመድ ግብ አድርጎት መድንን ወደ አቻነት መልሷል።

በመጠኑ እየተቀዛቀዘ በሄደው ጨዋታ በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ለመውሰድ ብርቱ ፉክክር ቢደረግበትም በሁለቱም በኩል የሚደረጉ የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ውጤታማ አልነበሩም። ሆኖም 20ኛው ደቂቃ ላይ ጉዳት ባስተናገደው ጄሮም ፊልፕ ምትክ አለን ካይዋን ቀይረው ያስገቡት ኢትዮጵያ መድኖች 36ኛው እና 38ኛው ደቂቃ ላይ በወገኔ ገዛኸኝ ከሴኮንዶች በኋላ ደግሞ በአለን ካይዋ አማካኝነት ሙከራ ማድረግ ችለው ነበር።

በአጋማሹ የመጨረሻ ደቂቃዎች በመጠኑ በመነቃቃት በቁጥር እየበዙ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን ለመድረስ ጥረት ያደረጉት መቻሎች 34ኛው ደቂቃ ላይ በአቤል ነጋሽ ካደረጉት የተሻለ ሙከራ በኋላ 41ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ለማስቆጠር ተቃርበው ነበር። ከነዓን ማርክነህ ከዮሐንስ መንግሥቱ ጋር ተቀባብሎ ያደረገው ሙከራ በግቡ የግራ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶበታል። ይህም የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው ወደ ዕረፍት አምርቷል።

ከዕረፍት መልስ መቻሎች 51ኛው ደቂቃ ላይ ግሩም ሀጎስ ከሳጥን አጠገብ ሞክሮት በግቡ የግራ ቋሚ በወጣው ኳስ እና 53ኛው ደቂቃ ላይ ምንይሉ ወንድሙ ከሳጥኑ የግራ ክፍል ሊፈጥረው ሞክሮ ተከላካዮች ተረባርበው ካመከኑበት ኳስ ውጪ የግብ ዕድሎች ሳይፈጠሩ ጨዋታው ዘለግ ላሉ ደቂቃዎች ቀጥሏል።


ኢትዮጵያ መድኖች እንዳላቸው የኳስ ቁጥጥር እና የማጥቃት እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ሲቸገሩ ይባስ ብሎም 74ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ሳጥናቸው የተላከውን ኳስ ያልተመጣጠነ ኃይል ያስተናገደው ሚሊዮን ሰለሞን በጫና ውስጥ ሆኖ በጭንቅላቱ ገጭቶት በግቡ የቀኝ ቋሚ በኩል ለጥቂት ወጥቶ ግብ ከማስተናገድ ተርፈዋል።

በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ተጭነው የተጫወቱት መቻሎች 89ኛው ደቂቃ ላይ ከነዓን ማርክነህ በሳጥኑ የቀኝ ክፍል ሲገባ ሚሊዮን ሰለሞን ጎትቶ ጥሎት በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ በላይ ታደሰ እምነት የተከለከለው የፍጹም ቅጣት ምት ጥያቄያቸው ከፍተኛ የነበር ሲሆን ጨዋታው ሊጠናቀቅ በተጨመሩ 7 ደቂቃዎች ውስጥ 4ኛው ደቂቃ ላይ መድኖች ግብ አግኝተዋል። መስፍን ዋሼ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ የመቻሉ ተከላካይ ነስረዲን ኃይሉ ሊያወጣው ሲሞክር የራሱን ግብ የላይ አግዳሚ ገጭቶ ሲመለስ ኳሱን ያገኘው አብዱልከሪም መሐመድ በግንባሩ በመግጨት ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አድርጎታል። ጨዋታውም በኢትዮጵያ መድን 2ለ1 አሸናፊነት ተጠናቋል። ድሉም ለኢትዮጵያ መድን ከ12 ጨዋታዎች በኋላ የተገኘ ሆኗል።

ከጨዋታው በኋላ በተሰጡ አስተያየቶች የኢትዮጵያ መድኑ አሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ ያሳኩት ድል ከነበረባቸው የድል ረሃብ አንጻር ትልቅ የስነልቦና ከፍታ እንደሚፈጥርላቸው በመጠቆም ወደ አሸናፊነት መምጣታቸው ትልቅ የደስታ ስሜት እንደፈጠረባቸው ተናግረው ላለመውረድ ከሚደረገው ትንቅንቅ በራሳቸው ዕድል ለመራቅ መወሰን እንዳለባቸው ገልጸው ለቀጣይ ጨዋታ የተከላካይ መስመራቸው ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርጉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል። የመቻሉ ምክትል አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሐዬ በበኩላቸው በጨዋታው መምራት ቢችሉም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር እንደተቸገሩ ተናግረው በዳኝነቱ ላይ ቅሬታ እንዳላቸው በመናገር ያለፈው ጨዋታ ላይ ቅሬታ ያቀረቡበት ዳኛ ዛሬ በድጋሚ ጨዋታቸውን መዳኘቱ ልክ እንዳልሆነ አበክረው አስታውቀዋል።