የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ21ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የ21ኛው ሳምንት ጨዋታዎችን መነሻ በማድረግ ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አደራደር 4-1-2-3


ግብ ጠባቂ

ሰዒድ ሀብታሙ – አዳማ ከተማ

በዚህ የጨዋታ ሳምንት በወጥነት የነጠረ ብቃት ካሳዩ ግብ ጠባቂዎች እንደ ሰዒድ ሀብታሙ ማግኘት አይቻልም። ቡድኑ ኢትዮጵያ ቡናን ባሸነፈበት ጨዋታ ዕረፍት የለሽ በሆነው የቡናማዎቹ ጥቃት በምድርም በሰማይ ቢሰነዘርበትም በሚገርም ንቃት እና ቅልጥፍና ሲያመክን የነበረበት መንገድ አስደናቂ ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ሰዒድ ቡድኑን ለመልሶ ማጥቃት አጨዋወት የሚያዘጋጅበት መንገድ በቦታው ያለ ምንም ተቀናቃኝ ተመራጭ ያደርገዋል።

ተከላካዮች

አብዱልከሪም መሐመድ – ኢትዮጵያ መድን

ኢትዮጵያ መድን ከ12 ጨዋታዎች በኋላ ከድል ረሃቡ ጋር በታራቀበት ጨዋታው የታታሪው የመስመር ተከላካይ ሚና ድንቅ ነበር። አብዱልከሪም የመቻልን የማጥቃት እንቅስቃሴ ከማቆሙ ባሻገር ከኳስ ጋር የነበረው ምቾት እንዲሁም በአስገራሚ ሁኔታ ቡድኑ ያሸነፈባቸውን ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ቡድኑን ውጤታማ በማድረግ የተሳካ ምሽት አሳልፏል። በተለይ በመጨረሻው ደቂቃ የተቆጠረችው ወሳኝ ጎል በሚገርም ሁኔታ በቦታው የተገኘበት መንገድ የመስመር አጥቂ እንጂ ተከላካይ አይመስልም ነበር።

ጊት ጋትኮች – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና ከመመራት ተነስቶ የሀድያ ሆሳዕናን ለአስራ ስምንት ሳምንታት የቆየውን ያለመሸነፍ ጉዞን በገቱበት ጨዋታ በመከላከሉ ረገድ ጊት የነበረው ድርሻ ከፍ ያለ ነው። የሀድያ ሆሳዕናን ተሻጋሪ ኳሶች ከመቆጣጠር ባለፈ በአንድ ለአንድ ግንኙነት የፊት አጥቂዎቹ ለመፍጠር የሚሞክራቸውን የጥቃት መነሻዎች በአግባቡ ሽፋን በመስጠት ያደረገው የመከላከል ትጋት እንዲሁም ቡልቻ ሹራ ላስቆጠራት ግብ አመቻችቶ በማቀበሉ በምርጥ አስራ አንድ ስብስብ ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

ፍቅሩ ዓለማየሁ – አዳማ ከተማ

በሊጉ በየጨዋታዎቹ መሻሻል ካሳዩን እና በጥሩ አቋም ላይ ከሚገኙ ተከላካዮች ውስጥ አንዱ የሆነው ፍቅሩ ዓለማየሁ ግሩም ምሽትን አሳልፏል። አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን1-0 ሲያሸነፍ ፍቅሩ በጥቅሉ በጥሩ ንቃት ከመንቀሳቀሱ ባለፈ በጥሩ ቅልጥፍና በሸርቴዎቹ ኳስ የሚያስጥልበት እና የአየር ኳሶችን በማውጣት የቡናን ማጥቃት እንቅስቃሴ ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን ያለ ዕረፍት ቦታው የሸፈነበት ሁኔታ ምርጫ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።

አብዱልሰላም የሱፍ – ሀምበርቾ

በሃያ አንደኛው ሳምንት በሊጉ በተደረጉ ጨዋታዎች አስገራሚ ብቃታቸው ካሳዩን ተጫዋቾች መካከል ተስፋኛው ወጣት አብዱልሰላም የሱፍ አንዱ ነው። ምንም እንኳን ቡድኑ በመጨረሻው ደቂቃ ዐፄዎቹ ባስቆጠሩት ጎል ነጥብ ተጋርቶ ቢወጣም በግሉ ጥሩ ቀን አሳልፏል። ከተሰጠው የመከላከል ሚናው ባለፈ በማጥቃቱ የጎላ ሚና የነበረው የግራ እግሩ ተጫዋች አብዱልሰላም ለፊት ተሰላፊዎቹ ከፈጠረው ምቾት ያላቸው ኳሶች ባሻገር አንድ ጎል በስሙ በማስቆጠሩ እንዲሁም ሳማኬ ሚኬል በራሱ ላይ ላስቆጠራት ግብ ቁልፍ መነሻ የነበር በመሆኑ ያለ ተቀናቃኝ በስብስባችን ለመጀመርያ ጊዜ በምርጫ ውስጥ እንዲካተት ሆኗል።

አማካዮች

ሀብታሙ ሸዋለም – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሀዋሳ ከተማን ከመመራት ተነስቶ 2-1 በመርታት እና ወደ ሊጉ በመጣበት ዓመት ዋንጫውን ከፍ አድርጎ ለማንሳት በሚያደርገው ግስጋሴ ውስጥ የተከላካይ አማካይ የሐብታሙ ቡድኑ መሐል ሜዳ ላይ ብልጫ እንዳይወሰድበት የነበረው አስተዋፆኦ የጎላ ነበር። ምንም እንኳን ቡድኑ ሁለተኛውን ጎል ካስቆጠረ በኋላ በሀዋሳ ብልጫ ቢወሰድበትም ከኳስ ውጪም ጥሩ በመሆን እና ስኬታማ ቅብብሎችን በማድረግ ባሳየው ትጋት በቦታው ተመራጭ አድርገውታል።

ፉዓድ ፈረጃ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ከተጠባባቂ ወንበር እየተነሳ ያለፉትን ጨዋታዎች ለቡድኑ ግልጋሎት እየሰጠ የሚገኛው ፉዓድ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ወደ መጀመርያ አሰላለፍ በመምጣት ጥሩ ጊዜ እያሳለፈ ይገኛል። ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከመመራት ተነስቶ ሀዋሳ ከተማን 2ለ1 ሲያሸንፍ የአማካዩ ሚና የጎላ ነበር። ፉዓድ ሳይመን ፒተር ላስቆጠራት ግብ ከቅጣት ምት ቁልፍ መነሻ የነበር ሲሆን ኪቲካ ጅማ ላስቆጠራት ግብም በግሩም ሁኔታ አመቻችቶ ማቀበል ችሏል። ይልቁንም እርሱ ተቀይሮ ከወጣ በኋላ የቡድኑ የማጥቃት ሚዛኑ የተቀዛቀዘ ሲሆን በአጠቃለይ በቆየባቸው ደቂቃዎች ያሳየው ጥሩ እንቅስቃሴ በስብስባችን እንዲካተት አስችሎታል።

አብዱልከሪም ወርቁ – ኢትዮጵያ ቡና

ቡናማዎቹ በአዳማ ከተማ 1ለ0 ሲሸነፉ የአማካያቸው ብቃት እጅግ አስደናቂ ነበር። አብዱልከሪም በተከታታይ ጨዋታዎች የሚያሳየው ብቃት በብዙዎች አድናቆት እያስቸረው ይገኛል። የኢትዮጵያ ቡና አባካኝነት ጎልቶ በታየበት ጨዋታ አብዱልከሪም በርካታ ያለቀላቸው የግብ ዕድሎችን ለቡድን አጋሮቹ አመቻችቶ ከማቀበሉም ባሻገር ያደረገው ዕረፍት የለሽ የሆነ ሳቢ እንቅስቃሴ በምርጥ 11 ቡድናችን ውስጥ በተከታታይ ሳምንት እንዲካተት አስችሎታል።

አጥቂዎች

ቡልቻ ሹራ – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡና የሀዲያ ሆሳዕናን ለ18 ተከታታይ ጨዋታ ያለመሸነፍ ጉዞ ሲገቱ የመስመር አጥቂው ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል። ቡልቻ ምንም እንኳን ቀድሞ ከነበረው ጥሩ ብቃት የተቀዛቀዘ ቢሆንም አሁን ራሱን ለማግኘት እየታተረ ይገኛል። ሆኖም የመጀመሪያውን የቡድኑን ጎል በስሙ ማስመዝገብ ሲችል ለሁለተኛው የማይክል ኪፖሩል ጎልም አመቻችቶ ማቀበል መቻሉ በምርጥ 11 ቡድናችን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

ዮሴፍ ታረቀኝ – አዳማ ከተማ

በሳምንቱ ምርጥ ጨዋታ አዳማ ከተማ ኢትዮጵያ ቡናን 1ለ0 ሲያሸንፍ የማሸነፊያዋን ጎል ማስቆጠር የቻለው ዮሴፍ ቡድኑ በሚጠቃበት ጊዜም ወደኋላ እየተመለሰ በማገዝ ያደረገው ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ወሳኝ የነበር ሲሆን ሁለተኛ ግብ ለማስቆጠርም እጅግ ተቃርቦ በግቡ የቀኝ ቋሚ ተመልሶበታል። ከዚህ በተጨማሪ ዮሴፍ ዓምና ለአዳማ በውድድር ዓመቱ ስምንት ጎሎችን በማስቆጠር ቀዳሚው ተጫዋች የነበር ሲሆን ዘንድሮ ዘጠነኛ ጎሉን በማስቆጠር የራሱን ሪከርድ አሻሽሏል።

ማይክል ክፕሮቪ – ሲዳማ ቡና

በተከታታይ ጨዋታዎች እንደ ቡድን አጋሩ ቡልቻ ሁሉ ራሱን ፈልጎ ለማግኘት እየታተረ የሚገኘው ማይክል ቡድኑ ሀዲያ ሆሳዕናን ከመመራት ተነስቶ ሲያሸንፍ የነበረው ሚና በጉልህ የሚታይ ነበር። ጋናዊው አጥቂ ለቡድኑ ጠንካራ የማጥቃት እንቅስቃሴ ማድረግ ሲችል የቡድኑን የማሸነፊ ወሳኝ ጎልም በስሙ ማስመዝገብ መቻሉ በቦታው የሳምንቱ ምርጥ 11 ስብሰባችን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

አሰልጣኝ ዘላላም ሽፈራው – ሲዳማ ቡና

ሲዳማ ቡናዎች ከመመራት ተነስተው ሀዲያ ሆሳዕናን 2ለ1 ሲያሸንፉ የሲዳማው አሰልጣኝ ዘላለም ሽፈራው ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ ያደረጉት የአደራደር ለውጥ እጅግ ወሳኝ ነበር። በተለይም ቡድኑ ከመመራት ተነስቶ ወደ መምራት ከተሸጋገረ በኋላም በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ጫና በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ ሳጥን በቁጥር በዝቶ በመጠጋት ጨዋታውን ለመቆጣጠር የመረጡበት መንገድ የነብሮቹን ለ18 ጨዋታዎች የዘለቀ ያለመሸነፍ ጉዞ ለመግታት ያስቻለ ነበር። በዚህም ዋና አሰልጣኙ ከአሰልጣኝ ገብረመድን ኃይሌ እና ከአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ ጋር ተፎካክረው ይህንን ምርጥ ቡድናችንን እንዲመሩ መርጠናቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ፍሬው ጌታሁን – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ሱሌይማን ሀሚድ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ቶሎሳ ንጉሤ – ሀምበርቾ
ብርሃኑ አሻሞ – ሀምበርቾ
በረከት ጥጋቡ – ባህር ዳር ከተማ
ብዙዓየሁ ሰይፉ – ወላይታ ድቻ
አማኑኤል ዮሐንስ – ኢትዮጵያ ቡና
ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ – ፋሲል ከነማ
ቸርነት ጉግሳ – ባህር ዳር ከተማ
ኪቲካ ጅማ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ