ታክቲካዊ ትንታኔ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 1-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

በ7ኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የአምናው ቻምፒዮን ቅዱስ ጊዮርጊስ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል፡፡ የሶከር ኢትዮጵያው ሚልኪያስ አበራ ጨዋታውን ተከታትሎ ይህንን ታክቲካዊ ትንታኔ አሰናድቷል፡፡

ሁለቱም ቡድኖች ካለፉት ጨዋታቸው ካሰለፏቸው ቋሚ ተሰላፊዎች መጠነኛ ለውጥን አድርገው በጀመሩት የምሽቱ ጨዋታ ባለሜዳ ሆኖ የተጫወተው ንግድ ባንክ 4-2-3-1 ፎርሜሽንን የተገበረ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊሶች ደግሞ 4-4-2 (በጨዋታ ሒደት ወደ 4-1-3-2 የሚቀየር) የተጫዋቾች የሜዳ ላይ አደራደርን ተጠቅመዋል፡፡ እነዚህን ፎርሜሽኖች ቡድኖች የተጠቀሙት በጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ ነው፡፡ ከእረፍት መልስ የጨዋታው ታክቲክ ለውጥም የተጫዋቾች ቅያሬም እንደነበር ልብ ይሏል፡፡

(ምስል 1)

Bank 1-1 Giorgis (1)

የጊዮርጊሶች ተጭኖ የመጫወት ዘዴ (pressing system)

ቅዱስ ጊዮርጊሶች በትናንት ምሽቱ ጨዋታ የኳስ ቁጥጥርም የሜዳላይ የበላይነትም ነበራቸው፡፡

ለዚህ ደግሞ ዋነኛ መሳሪያቸው ተጭኖ የመጫወት ስላታቸው አይነተኛ አስተዋፆ ነበረው፡፡

በተለይ የባንክን ጠንካራ ጎን የቀኝ መስመሩን ተከላካይ አዲሱን ሙሉ በሙሉ ወደፊት እየሄደ ተፅዕኖ የሚፈጥረው የማጥቃት አጨዋወቱን (over lap ማድረጉን) እንዲያቆም የኢሞቤንጎ pressing (ተጭኖ መጫወት ) ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው፡፡ ከፊቱ የነበረው ዋለልኝ ገብሬም ከአዲሱ ጋር የነበረው ርቀት ይበልጥ ወደኃላ እንዲመለስና የጊዮርጊሱ የግራ መስመር ተከላካይ ዘካርያስ ቱጂ በነፃነት ሰፊ ርቀትን ወደፊት እንዲጓዝና አማካይ ክፍሉን እና ዳዋ ኢቲሳን እንዲረዳ አድርጎታል፡፡ ይህን የባንኩ ሰለሞን ገ/መድህን በቀኝ የጎንዮሽ ክፍል ብዙ ቦታን እንዲሸፍን አስገድዶታል፡፡ ባንኮች በዚህ አመት በማጥቃት አጨዋወታቸው በተደጋጋሚ እንዲታየው አዲሱ ዋነኛ መሳሪያቸው ነበር፡፡ የአምናው የሊጉ ቻምፒዮኞች ይህንን መስመር መቆጣጠር መቻላቸው በጨዋታው ለነበራቸው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት አግዟቸዋል፡፡

ንግድ ባንኮች በግራ መስመር ላይ ዘንድሮ በበመስመር አማካይነት ሲሰለፍ የነበረው ሲሳይ ቶሊን በመስመር ተከላካይነት መጠቀማቸው ሌላው የቡድኑ ለውጥ ነበር፡፡ ሲሳይ ቶሊን በግራ መስመር ተከላካይነት እንዲሁም ኤፍሬም አሻሞን በመስመር አማካይነት የተጠቀሙት አሰልጣኝ ፀጋዬ በዚህኛው መስመር የሚኖራቸውን የማጥቃት እንቅስቃሴ የተሻለ ቢያደርጉትም በመከላከሉ ላይ ግን ችግሮች ተስተውለዋል፡፡ የሲሳይ የተጫዋችነት ባህሪና ምን አልባትም የተሰጠው የሜዳ ላይ ሚና ባብዛኛው ከመከላከሉ ይልቅ በማጥቃቱ ላይ በማተኮሩ ጥሎት የሚሄደውን ክፍተት በቦታው የነበረውና በ inverted winger ነት ሚና በቀኝ መስመር የተሰለፈው ምንያህል ተሾመ በአግባቡ ሲጠቀምበት ነበር፡፡ በዚህም ምክኒያት ኤፍሬም አሻሞ የሚታወቅበት ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ተገድቦ አምሽቷል፡፡ ምክኒያቱም ኤፍሬም ወደ ኃላ ተመልሶ የመከላከል ኃላፊነት ነበረበት፡፡ ቢያድግልኝ ኤልያስም የበለጠ ወደፊት የመጠጋት ነፃነት (overlap የማድረግ እድል) አግኝቷል፡፡ ንግድ ባንኮች በማጥቃት እንቅስቃሴያቸው የአማካይ ተከላካዮቻቸው ስንታለምና ታዲዮስ ወደፊት ሲጠጉ የተከላካይ መስመሩ ወደ ኋላ መቅረቱ በተደጋጋሚ በተከላካዮችና በአማካዮች መካከል ያለው ክፍተት (Between the lines) የበለጠ ክፍት ሆኖ ታይቷል፡፡

ዳዊ ኢቲሳ በ9ኛው ደቂቃ በዚህ አደገኛ የሜዳ ክልል ለአዳነ ግርማ በግንባር ገጭቶ ያዘጋጀለት ኳስ አዳነ በበታው ባለመገኘቱ ቢመክንም አጥቂው ክፍተተን ለመጠቀም ያደረገው ጥረት ትልቅ ነው፡፡

በተጨማሪም አዳነ የባንኮችን የመሃል ተከላካዮች በመጫን (press በማድረግ) ለቡድናቸው (depth) የሰጡት ሲሆን ባንኮች በHigh line defence ወደ መሃለኛው የሜዳ ክልል ቀርበው እንዳይከላከሉ በማድረግ በተጫዋቾች መካከል ያለውን ርቀት አስፍተዋል፡፡

አዳነ በጊዮርጊሶች የመከላከል የጨዋወት ላይ (defending phase) ከነስታለምና ታዲዮስ ፊት በመገኘትም አስተዋፆ የጎላ ነበር፡፡ይህም ምንያህል ወደ መሃል እየገባ (cut inside ቢያድግልኝ overlap እያደረገ እና ናትናኤል ዘለቀ በጎንዮሽ የቢያድግልኝን ክፍተት እየሸፈነ በጥሩ መግባባት ከቡድኑ ጋር ሲጫወት አምሽቷል፡፡ ዳማ ኢቲሳ በሜዳው በብዙ አቅጣጫዎች እየተገኘ ለጓደኞቹ የመቀባበያ አማራጮችን ሲፈጥር ነበር፡፡ ይህም ቡድኑ በተለያዩ ተጫዋቾች አማካኝነት ጥሩ ጥሩ የጎል ሙከራዎችን እንዲያደርግ አግዞታል፡፡ ከሲሳይ ቶሊ የሚያገኘውን ክፍተት ቢያድግልኝ ከመስመር በማሻማት ለአጥቂዎች የሚያደርሳቸው ኳሶች አደገኛ ነበሩ፡፡

(ምስል 2)

Bank 1-1 Giorgis (2)

የአሉላ ተፅዕኖ

መጠቀስ ካለባቸው የጨዋታው ዋነኛ ነጥቦች አንዱ ይህ ነው፡፡ በቀኝ መስመር ተከላካይነት ሚናው የሚታወቀው የፈረሰኞቹ 6 ቁጥር በጨዋታው የነበረው ሁለገብ ሚና (versatility role) የጎላ ነበር፡፡ ናትናኤል ዘለቀ በነፃነት ወደ ፊት እየሄደ በማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ቀጥተኛ ተስትፎ እንዲያደርግ ከማስቻሉ በላይ በሁለቱም የሜዳው መስመሮች (በቀኝም በግራም) በመገኝት የመቀባበያ አማራጮችን በማብዛት (passing lane options) የማጥቃት ማዕዘናትን በመጨመር ወይም በማስፋት (Attacking angles) እንዲሁም በመስመሮች የሚደረግን የጨዋታ ሽግግር (flank transition) በመምራት ለቡድኑ ጥሩ የጨዋታ አቀጣጣይነት ሚና (play making role) ሲወጣ ነበር፡፡ ለናቲ ያቀበለው ኳስም ጊዮርጊስን መሪ አድርጋ ነበር፡፡

ከአሉላ ጋር በተደጋጋሚ ቦታ በመቀያየርም የባንክን የመከላከል ቅርፅ ለማበላሰሸት የተሳካ ሙከራ አድርገዋል፡፡

(ምስል 3)

Bank 1-1 Giorgis (3)

2ኛው አጋማሽ

ንግድ ባንኮች በዚህኛው አጋማሽ የተጫዋቾችና የታክቲክ ለውጥ በመተግበር የተሻለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ተፈጥሮአዊውን የግራ መስመር ተከላካይ አለምነህ አስገብተው ሲሳይ ቶሊን ወደ ግራ መስመር አማካይነት ፤ ዋለልኘ ገብሬን አስወጥተው ኤፍሬም አሻሞን ወደ ቀኝ መስመር አማካይነት አሸጋሽገዋል፡፡ ስንታለምንም በታዬ አስማረ ተክተው ወደ 4-1-4-1 አጨዋወታቸውን በመቀየር የተጋጣሚያቸውን የመሃል ሜዳ የበላይነት ለመቆጣጠር ሞክረዋል፡፡ ብራዚላዊው የቀድሞ የጃሜይካ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ኔይደር ዶሳንቶስም ከዕረፍት መልስ (በባንክ ለውጥ ላይ ተመስርተው ይመስላል) ወደ 4-3-4 ተሸጋገሩ፡፡ አዳነ በመሀል አጥቂነት ( እስከ ተቀየረበት ሰዓት ድረስ) ዳዋ በግራ (wide for wards) ሚና ኢምቤንጎ ደግሞ በቀኝ ፡፡ ፍፁም ገ/ማርያም በ76ኛው ደቂቃ በአዳነ ሲተካም ኢምቤንጎና ምን ያህል ቦታ በመቀያየር ከሚፈጥሩት ለውጥ ውጪ የተለየ ቅርፅ አልታየም፡፡ ንግድ ባንኮች በኤፍሬም አማካኝነት ዘካርያስን ተጭነው መጫወታቸው የጠቀማቸው ይመስላል፡፡ ዘካሪያስ ከእረፍት በፊት እንደነበረው ነፃነት ያልነበረው ሲሆን ከማጥቃቱ ይበልጥ ወደ መከላከሉ ማዘንበሉ ለፀጋዬ ልጆችም ጫናቸው የቀነሰ ነበር፡፡ ሲሳይ ቢያድግልኝን አለምነህ ኢምቤንጎን press ማድረጋቸው የማጥቃትና መከላከል እንቅስቃሴያቸው ላይ ተፅዕኖ አሳርፏል፡፡ በዚህም በ88ኛው ደቂቃ ላይ ዘካሪያስ ኤፍሬም ላይ በስራው ጥፋት የተገኘችውን ፍፁም ቅጣት ምት ፊሊፕ ዳውዚ በጥሩ ሁኔታ ሊያስቆጥራት ችሏል፡፡ በዕለቱ ብዙም ጥሩ ሲንቀሳቀስ ያልታየው የንግድ ባንኩ አጥቂ ጫላ ድሪባ እስከ 65ኛው ደቂቃ ድረስ ሜዳ ውስጥ መቆየቱ ቡድኑ ከፊሊፕ የሚያገኘውን ጥቅም ያሳጣው ይመስለኛል፡፡ ዳውዚ Highline የሚሰሩ ተከላካዮች ያላቸው ቡድኖች ላይ የሚፈጥረው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ታይቷል፡፡ ናይጄሪያዋው አጥቂ ለቡድኑ Depth በመስጠትና ከተከላካዮች ጀርባ ያለውን ክፍተት በመጠቀም የተሻለ ብቃት እንዳለው በተደጋጋሚ በጨዋታዎች አሳይቷል፡፡

(ምስል 4)

Bank 1-1 Giorgis (4)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *