ዮሃንስ ሳህሌ የደደቢት አሰልጣኝ ሆነው ተሾሙ

በ2006 አ.ም የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሄራዊ ቡድንን ያሰለጠኑት ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ የደደቢት እግርኳስ ክለብን ለማሰልጠን ከስምምነት ደርሰዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊው ደደቢት ዘንድሮ የመጀመርያዎቹን 3 ተከታታይ ጨዋታዎች በማሸነፍ ድንቅ ጅማሬ ቢያደርግም ያለፉትን 3 ተከታታይ ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳያስቆጥር መሸነፉን ተከትሎ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታን ከአሰልጣኝነት ማንሳቱትን ትላንት አስታውቋል፡፡

ንጉሴ ደስታ የ3ወር ደሞዝ ተሰጥቷቸው ከክለቡ ጋር የተለያዩ ሲሆን እንደ ክለቡ አመራሮች ገለፃ ከቡድኑ ወቅታዊ የውጤት ቀውስ በመነሳት በ2006 ዓ.ም. የታየው የውጤት ቀውስ እንዳይደገም በመፍራት አሰልጣኙን አሰናብተዋል፡፡ ይህንን ተከትሎ ከዚህ በፊት ለአጭር ጊዜ የደደቢት እግርኳስ ክለብ ቴክኒካል ዳይሬክተር ሆነው ያገለገሉት ዮሃንስ ሳህሌ በጊዜያዊነት ሰማያዊውን ጦር ተረክበዋል፡፡

አሰልጣኙ ከሹመታቸው በኋላ ዛሬ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት “ኮንትራቱ ክፍት ነው፡፡ የቅጥር ሁኔታው አስከዚህን ያህል ጊዜ የሚል አይደለም፡፡ በ6 ወር ወስጥ የሚሻሻ ሉ እና የሚጨመሩ ነገሮች ይኖሩታል፡፡ የክለቡ ግብ በአፍሪካ ኮንፌድሬሽንስ ካፕ ከዚህ በፊት ከተጓዘበት መንገድ በላይ መጓዝ ነው፡፡ በፕሪምየር ሊጉም እከመጨረሻው ጊዜ ድረስ ተፎካካሪ ሆኖ መቅረብ እንፈልጋለን፡፡ ሻምፒዮን መሆንን ጨምሮ ማለቴ ነው፡፡ ›› ሲሉ የኮንትራት ጊዜያቸው ከውጤታማነታቸውና ከክለቡ የዘንድሮ እቅድ አንፃር እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

ኢንስትራክተር ጨምረውም ከቀድሞ አሰልጣኝ ጠንካራ ጎኖችን ወስደው የራሳቸውን ፍልስፍና በቡድኑ ውስጥ ለማስረፅ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ ክለቡ ለ1 ዓመት ከግማሽ ለሆነ ጊዜ በአንድ አሰልጣኝ ሰልጥኗል፡፡ ይህ አሰልጣኝ የሰራውን ቡድን እንዲሁ ዝም ብለህ አትለውጠውም፡፡ ስለዚህ መሻሻል ያለባቸውን ነገር በማሻሻል ውጤታማ መሆን ነው ቀዳሚ አላማችን፡፡ ያሉትን ጠንካራ ጎኖች በማስቀጠል እንዲሁም የራሴን የአሰለጣጠን ፍልስፍና በመከተል ውጤታማ መሆን እፈልጋለሁ” ብለዋል፡፡

ኢንስትራክተር ዮሃንስ ሳህሌ ፋክት

በተጫዋችነት የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ፣ የራስ ሆቴል እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብን በ1970ዎቹ አገልግለዋል፡፡

ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር በ1976 የኢትዮጵያ ሻምፒዮን ሆነዋል

የእግርኳስን አሰልጣኝነትን በሆላንድ፣ ጀርመን፣ ብራዚል እና ዩናይትድ ስቴትስ ተምረዋል፡፡

በቴክኒካል ዳይሬክተርነት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽንን እንዲሁም የደደቢት እግኳስ ክለብን አገልግለዋል፡፡

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *