ለኢትዮጵያ እግርኳስ አፍቃሪያን አዲስ ስም አይደለም ፡፡ ናይጄሪያዊው የ26 ዓመት አጥቂ ለመብራት ኃይል፣ ለደደቢት ተጫውቶ አሳልፏል፡፡ አሁን ደግሞ ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በመጫወት ይገኛል፡፡ ፊሊፕ ስለ እግርኳስ ህይወቱ ከሶከር ኢትዮጵያው ኦምና ታደለ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር፡፡
ፊሊፕ ዳውዚ የተወለደው በናይጄሪያዋ የደቡብ ምዕራብ ከተማ ሌጎስ በ1981 ነበር ፡፡ ሁለት ወንድሞች እና አንድ እህት ያለችው ፊሊፕ በእግርኳስ ፍቅር መለከፍ የጀመረው በእናቱ ማህፀን መሆኑን ይናገራል፡፡ “እግርኳስን መጫወት የጀመርኩት ገና በእናቴ ማህፀን ሳለው ነው፡፡ በ5 ዓመቴ እግርኳስን በደንብ መጫውት ጀምሬ ነበር፡፡”
እንደ አብዛኞቹ የተጫዋች ቤተሰቦች ፊሊፕ ከወላጆቹ እግርኳስን እንዳይጫወት ተፅዕኖ ደርሶበት ነበር፡፡ ወላጅ አባቱ መሀንዲስ በመሆናቸው ልጃቸውም ወደ ትምህርቱ እንዲያተኩር ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፡፡ “ወላጅ አባቴ ልክ እንደሱ መሀንዲስ እንድሆን ይፈልግ ነበር፡፡ አባቴ እግኳስን ፈፅሞ አይወድም፡፡ እግርኳስ ስጫወት የምጎዳ ስለሚመስለው እንድጫወት አይፈቅድልኝም ነበር፡፡ በትምህርቴ ጎበዝ እንድሆን እና የተሻለ ህይወት እንድመራ ነበር የሚፈልገው፡፡ የታክሲና ለትምህርት ወጪ ብሎ ገንዘብ አይሰጠኝም ነበር፡፡”
ፊሊፕ ከወላጅ የአባቱን ጫና ተቋቁሞ ፕሮፌሽናል እግርኳስ ተጫዋች ለመሆን ሲያልም ገና የ10 አመት ታዳጊ ነበር፡፡ የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለም ይህንን ህልሙን ለማሳካት ከፍተኛ ተነሳሽነት ነበረው፡፡ “10 ዓመት ልጅ እያለው እግርኳስን እንደስራ ማየት ጀመርኩ፡፡ በተለይ በሀገሬ ናይጄሪያ ተጨዋቾች ወደ አውሮፓ ሀገራት ሄደው ሲመለሱ ብዙ ብር ይዘው ይመጡ ነበር፡፡ መኪና እና ቆንጆ ቤት ነበራቸው፡፡ እነሱን ሳይ እግርኳስ ተጫዋች መሆን እንዳለብኝ ማሰብ ጀመርኩ፡፡”
ፊልፕ እግርኳስን መጫወት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ የፊት መስመር ተጫዋች ነበር፡፡ ይህንንም ሲናገር ፊቱ ላይ እርግጠኝነት ይነበባል፡፡ “ከመጀመሪያው ጊዜ ጀምሮ የአጥቂ መስመር ተጫዋች ነበርኩ፡፡ የፊት መስመር ተጫዋች ስትሆን ጎል በማስቆጠር ለሰዎች ደስታን ታመጣለህ፡፡ ሰዎች አንተ ጎል አስቆጥረህ ሲደሰቱ ማየት ደግሞ ከፍተኛ የስሜት እርካታን ይሰጣል፡፡ ለዚህም ነው የአጥቂ መስመር ተጫዋች የሆንኩት፡፡ ”
ናይጄሪያ የጎለበተ እግርኳስ ደረጃ አላቸው ከሚባሉት የአፍሪካ ሀገራት መካከል ቅድሚያ የሚሰጣት ሀገር ናት፡፡ የናይጄሪያ እግርኳስ ጥንካሬም ፊልፕ በናይጄሪያ እግርኳስን እንዳይጫወት እንዳገደው ያምናል፡፡ “ናይጄሪያ ውስጥ በክለብ ደረጃ አልተጫወትኩም፡፡ ለመጫወት ሰዎችን ማወቅ አለብህ ፣ ጥሩ እና ጎበዝ ተጫዋች መሆን አለብህ፡፡ እኔ ግን የጠበበ እድል ስለነበረኝ እግርኳስን ለመጫወት ወደ ሌላ ሀገር መሄድ ምርጫዬ አድርጊያለው፡፡” አዎ ፊልፕ ለሌጎስ በጣም ቅርብ ለነበረችው የቤኒንዎ ዋና ከተማ ፓርቶ ኖቭኦ ለሚገኘው ለዩኒየን ስፓርቲቭ ሰም ከራክ (Union Sportive Seme Krake) ፈረመ፡፡ በቤኒን የተሳካ ቆይታ ካደረገ በኅላ ወደ መካከለኛው ምስራቅ በመሄድ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ክለብ የሆነውን አል-ሸአብን ተቀላቀለ፡፡ በሻርዣህ ግዛት ለሚገኘው ክለብ ከተጫወተ በኋላ በአንድ ወኪል አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡
ፊሊፕ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበትን ጊዜ እንዲሀ ያስታውሰዋል፡ “አንድ የማውቀው ወኪል ኢትዮጵያ መጥቼ እንድጫውት ጥያቄ አቀረበልኝ፡፡ በመጀመሪያ አቅማምቼ ነበር፡፡ ወኪሉ ለ3 ወራት ብቻ እንደምቆይ ስለነገረኝ ሀሳቤን ለውጬ ወደ ኢትዮጵያ ልመጣ ቻልኩ፡፡ በመጀመርያ በኢትዮጵያ ብዙ ጊዜ የመቆየት ሀሳቡ አልነበረኝም ፡፡ ነገር ግን ነገሮች መስመር በመያዛቸው ረጅም ጊዜ ልቆይ ቻልኩ፡፡” ፊሊፕ በዝውውሩ የሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ቻምፕዮኖቹን መብራት ሀይልን መቀላቀል ቻለ፡፡ ነገር ግን በመብራት ኃይል የፊሊፕ አጀማመር ቀዝቃዛ ነበር፡፡ በመጀመራያዎቹ ጨዋታዎች ላይ ግብ ሊያስቆጥር አልቻለችም ነበር፡፡
“ለመብራት መጫወት ስጀምር ግብ ማስቆጥር አልቻልኩም ነበር፡፡ ሀገሪቱ ለኔ አዲስ ነበረች፡፡ አየሩ በጣም ይከብድ ነበር፡፡ የመጀመሪያዋቹ ጥቂት ጊዜያት በጣም ከባድ ነበሩ፡፡” ምንም እንኳን ፊሊፕ ግብ አያስቆጥር እንጂ የክለቡ ደጋፊዎች ያበረታቱት ነበር፡፡ የደጋፊዎቹ ማበረታት በኢትዮጵያ ተደላድሎ እንዲቀመጥ አስተዋፅኦው ከፍተኛ እንደነበረም ያምናል፡፡ “ስሜን እየጠሩ አይዞ ሲሉኝ በውስጤ እነዚህን ደጋፊዋች መካስ አንዳለብኝ ይሰማኝ ነበር፡፡ ግብ ማስቆጠር ስጀምር የደጋፊዎች እገዛ ከፍተኛ ነበር፡፡ ነገሮችን በቀላሉ መልመድ ጀመርኩ፡፡ ምድሩን፣ ሰዉን እና ባህሉን መልመድ ጀመርኩ፡፡ በተለይ የሳሙኤል ሳኑሚ እና የኢማኑኤል ፌቮ ከጎኔ መኖር ነገሮችን በጣም አቀለሉት፡፡ ሳሚ እና ፌቮ የሀገሬ ልጆች ናቸው፡፡ አንድ ቋንቋ እንናገራለን፡፡ ይህም በጣም ረድቶኛል፡፡ አሰልጣኝ ዮርዳን ስቶይኮቭ ተጫዋች በጣም ይረዳ ነበር፡፡”
ቀስ በቀስ ፊሊፕ ዳውዚ በመብራት ሀይል መንገስ ጀመረ፡፡ በሱ ግቦች ታግዞ መብራት ኃይል ውጤታማ መሆን ጀመረ፡፡ ከሃገሩ ልጅ ሳሚ ሳኑሚ ጋርም ድንቅ ጥምረት መመስረት ጀመሩ፡፡ “የነበረን ስብስብ የተጠናከረ አልነበረም፡፡ ነገር ግን የአሸናፊነት ስነ-ልቡናችን ጥሩ የሚባል ነበር፡፡ ፍቅር በሁላችንም መሃል ነበረ፡፡” በትክክልም የፊሊፕ አቋም ከመብራት ኃይል ስብስብ ጎልቶ ወጣ፡፡ የ2004 የውድድር ዘመን ሲጠናቀቅም ፊሊፕ እና መብራት ኀይል መለያየታቸው እርግጥ ሆነ፡፡ “የ2004 ዓ.ም. የውድድር ዘመን ከመጠናቀቁ 3 ጨዋታዎች በፊት ነው ለደደቢት የፈረምኩት፡፡ ደደቢት የአፍሪካ ኮንፌድሬሽን ዋንጫ በ2005 ዓ.ም. ተሳታፊ በመሆኑ ለክለቡ ለመጫወት ወሰንኩ፡፡ በደሞዝ ደረጃም መብራት ከሚከፍለኝ የተሻለ እንደሚከፍሉኝ ነገሩኝ፡፡ ምንም ሳላንገራግር ደደቢትን ተቀላቀልኩ፡፡ በእርግጥ መብራት ኃይልን መልቀቅ ከባድ ነበር፡፡ በተለይ ደጋፊዎቹን በጣም ስለምወዳቸው ክለቡን መልቀቅ በጣም ከባድ ነበር፡፡ በመጨረሻው የውድድር ጨዋታ ላይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ጎል ካስቆጠርኩ በኅላ የመብራት ደጋፊዎች ጋር በመሄድ ተሰናብቻለሁ፡፡ ነገር ግን በመልቀቄ ውስጤ ሀዘን ተሰምቶት ነበር፡፡”
ፊልፕ በከፍተኛ የፊርማ ክፍያ ደደቢትን ተቀላቀለ፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገሮች በደደቢት አልጋ በአልጋ አልነበሩም፡፡ ከአሰልጣኝ አብረሃም ተ/ሃይማኖት ጋር በተደጋጋሚ መጋጨት ጀመረ፡፡ በክለቡ ከቀድሞው ባለቤት ኮ/ል አወል አብዱራሂም ጋር ጥሩ ግንኙነት ቢኖረውም ፊሊፕ በክለቡ ብዙም ሊቆይ አልቻለም፡፡ የጌታነህ ከበደ እና የዳዊት ፍቃዱ ጥሩ ብቃት ላይ መገኘት ፊልፕ የተሰላፊነት እድል እናዳያገኝ አግዶ ነበር፡፡ ስለደደቢት ቆይታው ስታነሱበት ፊቱ ላይ ደስተኝነት አይነበብበትም፡፡ በሰማያዊው ጦር ስላሳለፈው ጊዜ ሲናገርም አጭር እና ግልፅ በሆነ ቋንቋ ነው፡፡ “በኢትዮጵያ የእግርኳስ ቆይታዬ የፈፀምኩት ከባድ ስህተት ደደቢትን መቀላቀሌ ነበር፡፡” ፊልፕ ደደቢትን ከለቀቀ በኃላ በርካታ ክለቦች የፈርምልን ጥያቄ ማቅረብ ጀመሩ፡፡ ከነዚም ውስጥ የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ቡና ይገኝበታል፡፡ “ለቡና ለመጫወት እድሉ ቀርቦልኝ ነበር፡፡ ቢሆንም በገንዘብ ሳንስማማ ለቡና ሳልፈርም ቀረሁ፡፡ ለወደፊት ለቡና መጫወት እፈልጋለሁ፡፡”
የፊልፕ ቀጣይ ማረፊያ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ነበር፡፡ “የንግድ ባንክ ተጫዋቾች ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ አድርገዋል፡፡ አሁን ደደቢት ከነበርኩበት በተሻለ ደስተኛ ነኝ፡፡ ለኔ ንግድ ባንክ ቤቴ ሆኗል፡፡” ዘንድሮ በንግድ ባንክ 2ኛ ሙሉ የውድድር ዘመኑን የጀመረው ፊሊፕ ቡድኑ የአዲስ አበባን ሲቲ ካስትል ካፕን ዋንጫ እንዲያነሳ ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ በ7 ጨዋታዎች 4 ግቦች በማስቆጠር በግሉ ጥሩ አጀማመር ቢያደርግም ክለቡ ግን የተጠበቀውን ያህል መሆን አልቻለም፡፡ ፊሊፕም ስለ አዲሱ የውድድር ዘመን ፣ በበና ጨዋታ ላይ ስለተፈጠረው አጋጣሚ እና ስለቀዝቃዛ አጀማመራቸው ይናገራል፡፡ “ፕሪምየር ሊጉ ሲጀመር የገጠምነው ጠንካራውን ቡና ነበር፡፡ ጨዋታውን አሸንፈን በመውጣችንም ደስተኛ ነበርን፡፡ በዚም አጋጣሚ ቡና ላይ ካስቆጠርኩ በኃላ ባሳየሁት ድርጊት ያስቀየምኩት ሰው ካለ ይቅርታ እጠይቃለው፡፡ በመቀጠል ከወልዲያ ጋር ተጫወትን፡፡ ሜዳው አመቺ ባለመሆኑ አቻ ልንመጣ ችለናል፡፡ ከሙገር ጋርም በትኩረት ችግር ምክንያት አቻ ልንለያየን ችለናል፡፡ ነገሮችን ለማስተካከል እየሰራን እንገኛለን፡፡ በእግርኳስ የውጤት ማጣት ይከሰታል፡፡ ጠንክረን ሰርተን ወደ አሸናፊነታችን እንመለሳለን፡፡”
ፊሊፕ በኢትዮጵያ ከ4 አመታት በላይ ቆይቷል፡፡ ከኢትዮጵያ ባህል ፣ ህዝብ እና አኗኗር ጋርም በሚገባ ተላምዷል፡፡ “ኢትዮጵያን በጣም ወድጃታለሁ፡፡ ደስ የሚል ጊዜ እያሳለፍኩ እገኛለው፡፡ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ብድን የተጫወትልን ጥያቄ ከመጣ አትጠራጠር እጫወታለው፡፡ ህዝቡ ለእግርኳስ ያለው ፍቅር የሚገርም ነው፡፡ ስታዲየም ያለውን ድባብ ሳይ ሁልጊዜም ለኢትዮጵያ መጫወትን እመኛለው፡፡” ሲል ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የመጫወት ምኞቱን ይገልፃል፡፡
ፊልፕ ጠንካራ እና በቴክኒክ የበለፀገ አጥቂ በመሆኑ በሊጉ ተtከለካዮች እምብዛም አይፈተንም፡፡ ነገር ግን ፊሊፕ በተቃራኒነት ስለገጠሙት ተከላካዮች ሲናገር የሳላዲን በርጊቾን ስም በቅድሚያ ይጠራል፡፡ “ቀድሞ በመድህን አሁን ደግሞ በቅዱስ ጊዮርጊስ በተቃራኒነት የገጠምኩት ሳላዲን ባርጌቾ ካጋጠሙኝ ተከላካዮች ከባዱ ነው፡፡ በጣም ፈጣን ስለሆነ በጣም ያስቸግራል፡፡ በነገራችን ላይ ፈጣን ተከላካይ አልወድም፡፡ ተከላካይ ባይሆንም ዳዊት እስጢፋኖስን በጣም አደንቀዋለው፡፡ ለኔ የሊጉ ምርጥ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ዳዊት ነው፡፡”
ፊሊፕ በእግርኳስ አፍቃሪያን እና ጋዜጠኞች ዘንድ የቡድን ተጫዋች አይደለም እየተባለ ይተቻል፡፡ ነገር ግን በዚህ አስተያየት ፊሊፕ ሁሌም እንደሚገረም ይናገራል፡፡ “ይህንን እኔ አልቀበለውም፡፡ እኔ የቡድን ተጫዋች ነኝ፡፡ ግብ ከማስቆጠር ይልቅ የቡድን አጋሮቼን ማገዝ እወዳለሁ፡፡ ተመልከት አብዱልከሪም በዋንጫ ጨዋታ ላይ ኢትዮጵያ ቡና ላይ ጎል ያስቆጠርንበትን ኳስ አመቻቼ ያቀበልኩት እኔ ነበርኩ፡፡ እንደውም የቡድን አጋሬ ጫላ ድሪባ አጨዋወቴን ተመልክቶ አጥቂ ስትሆን ስግብግብ መሆን አለብህ ይለኛል፡፡ በእርግጥም አጨዋወቴን ያልተረዱ ሰዎች ብዙ ከመሆናቸው አንፃር የተነሳ የተሳሳተ ሃሳብ ይመስለኛል፡፡”
ፊልፕ በኢትዮጵያ ቆይታው ማሳካት የሚፈልጋቸው ነገሮች አሉ፡፡ “እንደማንኛውም ተጫዋች ዋንጫዋችን ማንሳት እፈልጋለው፡፡ በቋሚነት እግርኳስን መጫወት ህልሜ ነው፡፡”