የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ22ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በ22ኛው የጨዋታ ሳምንት ጎልተው በወጡ ተጫዋቾች ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አሰላለፍ 4-2-1-3

ግብ ጠባቂ

አብዩ ካሳዬ – ድሬዳዋ ከተማ

በከተማቸው እና በደጋፊዎች ፊት የሚያደርጉትን የመጨረሻ ጨዋታ ብርቱካናማዎቹ በድል ባጠናቀቁበት ጨዋታ የወጣቱ ግብ ጠባቂ አስተዋፆኦ በጉልህ የሚታይ ነበር። በየጨዋታዎቹ በሚያሳየው ትጋት የቡድኑ ቀዳሚ ተመራጭ መሆኑን እያረጋገጠ የመጣው ግብጠባቂው አብዩ የሻሸመኔን በርከት ያሉ ጥቃቶችን በጥሩ ቅልጥፍና ሲያመክን የዋለ ሲሆን ቡድኑ ላገኘው ወሳኝ ድል ከነበረው ሚና በመነሳት በምርጥ አስራ አንድ ውስጥ ሊካተት ችሏል።

ተከላካዮች

እንየው ካሳሁን – ሀዋሳ ከተማ

ሀዋሳ ከተማዎች በሀምበርቾዎች እጅግ ተፈትነው ሦስት ነጥብ ባሳኩበት ጨዋታ እንየው ካሳሁን በሁለቱም አቅጣጫ የመስመር ተከላካይ በመሆን መልካም አፈፃፀም አሳይቷል። ከመከላከሉ ባለፈ በማጥቃት ላይ የነበረው ተሳትፎ ጥሩ የነበረ ሲሆን በተለይ የሀምበርቾን ተደጋጋሚ ፈጣን የመስመር ማጥቃት እንቅስቃሴን በማቋረጥ ቡድኑ ላሳካው ሦስት ነጥብ የነበረው ድርሻ ከግምት በማስገባት በቀኝ በኩል ያለውን ቦታ ሰጥተነዋል።

ካሌብ አማንክዋህ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ወደ ሊጉ በመጣበት ዓመት በወጥ አቋም በማገልገል ቡድኑ ወደ ዋንጫው በሚያደርገው ግስጋሴ የጋናዊው የመሀል ተከላካይ አስተዋፆኦ እያደገ መጥቷል። ካሌብ በሜዳ ላይ ቆይታው ከህመሙ ጋር በመታገል ቡድኑ በሲዳማ ቡና የደረሰበትን ጫና እንዲቋቋም ጥሩ የተንቀሳቀሰ ሲሆን ከፈቱዲን ጀማል ጋር ጥሩ ጥምረት በመፍጠር ከኋላ ቡድኑን በብስለት በመምራት በጨዋታው ግብ እንዳይቆጠርበት ኃላፊነቱን ተወጥቷል።

ፍጹም ፍትሕዓለው – ባህር ዳር ከተማ

ከተጠባባቂ እየተነሳ የጣና ሞገዶቹ ወሳኝ ተከላካይ እየሆነ የመጣው ታዳጊው ፍጹም ቡድኑ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር ነጥብ በተጋራበት ጨዋታ የአንበሉ ያሬድ ባዬህን አለመኖር ተከትሎ በቋሚ አሰላለፍ ውስጥ በመካተት ግሩም እንቅስቃሴ አድርጓል። በተለይም በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ነብሮቹ ጥሩ የግብ ዕድል ፈጥረው ያቋረጠባቸው የሳሙኤል ዮሐንስ ውጤት ቀያሪ ሊሆን የሚችል ኳስ ተጠቃሽ ነው።

ኤፍሬም ታምራት – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ንግድ ባንክ ከፈረሰኞቹ ጋር ባደረጉት ጨዋታ ወቅት በመጨረሻው 20 ደቂቃ ተቀይሮ ከገባበት ጊዜ ወዲህ ከሚታወቅበት የግራ መስመር አጥቂነት ወደ መስመር ተከላካይነትን በአሰልጣኝ በፀሎት ሽግሽግ እንዲያደርግ የተደረገው ኤፍሬም የተረከበውን ወሳኝ ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ ይገኛል። ቡድኑ ሲዳማ ቡናን በረታበት ጨዋታ ከነበረው የመከላከል ጥንካሬ ባሻገር ወደ ፊት በመሄድ በመጨረሻው ደቂቃ ባሲሩ ላስቆጠራት ወሳኝ ጎል አመቻችቶ በማቀበሉ በምርጥ አስራ አንድ ስብስባችን ሊካተት ችሏል።

አማካዮች

ጃቢር ሙሉ – ፋሲል ከነማ

ዐፄዎቹ ከአዳማ ከተማ ጋር ያለ ግብ በተለያዩበት ጨዋታ ታዳጊው አማካይ የበርካታቶችን ትኩረት የሳበ ማራኪ እንቅስቃሴ አድርጓል። ከጨዋታው በፊት በ11 ጨዋታዎች 186 ደቂቃዎችን ሜዳ ላይ ማሳለፍ ችሎ የነበረው ጃቢር ሙሉ ለ84 ደቂቃዎች በተጫወተበት የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ አይጠቀምባቸው እንጂ በርካታ የግብ ዕድሎችንም መፍጠር ችሏል።

ባሲሩ ኦማር – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

በሁሉም የቡድኑ ጨዋታዎች ላይ መሳተፍ የቻለው ጋናዊው አማካይ ባሲሩ ንግድ ባንኮች ሲዳማ ቡናን 1ለ0 አሸንፈው መሪነታቸውን በአምስት ነጥቦች ልዩነት ሲያደርጉ ካደረገው ዕረፍት የለሽ እንቅስቃሴ ባሻገር የማጥቃት ሽግግሩን በማሳለጥ የቡድኑን ብቸኛ ግብም በግሩም አጨራረስ ማስቆጠር ችሏል።

አቡበከር ሳኒ – ኢትዮጵያ መድን

በአጋማሹ የዝውውር መስኮት ከወልቂጤ ከተማ ወደ ኢትዮጵያ መድን የተቀላቀለው የመስመር አጥቂው አቡበከር የቀድሞ ቡድናቸውን 3ለ0 በረቱበት የጨዋታ ሳምንት ፈታኝ የማጥቃት እንቅስቃሴዎችን በማድረግ እና ሁለት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል አንድ ግብም በስሙ ማስመዝገብ በመቻሉ ያለ ተቀናቃኝ በቦታው ተመራጭ ሆኖ በምርጥ 11 ቡድናችን ውስጥ ተካትቷል።

አጥቂዎች

ዘላለም አባተ – ወላይታ ድቻ

ወላይታ ድቻዎች ከስምንት ድል አልባ ጨዋታዎች በኋላ ጊዮርጊስን አሸንፈው የድሬዳዋ ቆይታቸውን ሲያገባድዱ የቡድኑን ብቸኛ ግብ ከሳጥን ውጪ በግሩም ሁኔታ ማስቆጠር የቻለው ዘላለም ከግቡ ባሻገር ያደረገው ጥሩ የማጥቃት እንቅስቃሴ በምርጥ 11 ቡድናችን ውስጥ እንዲካተት አስችሎታል።

ካርሎስ ዳምጠው – ድሬዳዋ ከተማ

ብርቱካናማዎቹ የመቀመጫ ከተማቸውን ቆይታ በድል ሲጨርሱ በተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ደምቆ ዕየታየ ያለው ካርሎስ ዳምጠው እንቅስቃሴ ወሳኝ ነበር። ተጫዋቹ በርካታ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ሲችል የቡድኑን የማሸነፊያ ግብም ከሳጥን ውጪ በደካማው የግራ እግሩ እጅግ አስደናቂ በሆነ ሁኔታ ከመረብ ላይ ማሳረፍ ችሏል።

ቢኒያም ፍቅሩ – ወላይታ ድቻ

የጦና ንቦቹ ፈረሰኞቹን ረትተው የድል ረሃባቸውን ባስታገሱበት ጨዋታ ከአራት ጨዋታዎች ቅጣት በኋላ ወደ ሜዳ የተመለሰው ቢኒያም ፍቅሩ ብቃት እጅግ የሚያስደንቅ ነበር። በተለይም በሁለተኛው አጋማሽ የተጋጣሚ ቡድን ተከላካዮችን በግሩም ክህሎት በማለፍ በርካታ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር በአንድ አጋጣሚም ግሩም ግብ ለማስቆጠር ተቃርቦ በግቡ የቀኝ ቋሚ ተመልሶበታል።


አሰልጣኝ ያሬድ ገመቹ – ወላይታ ድቻ

ከዚህ የጨዋታ ሳምንት በፊት በጉዳት እና በቅጣት በተመናመነው የቡድን ስብስባቸው ካደረጓቸው ስምንት ጨዋታዎች አራት ተሸንፈው አራት አቻ በመለያየት ከነበራቸው አስደናቂ ጉዞ የተቀዛቀዙ የነበሩት ወላይታ ድቻዎች ከናፈቃቸው ድል ጋር በታረቁበት የቅዱስ ጊዮርጊስ ጨዋታቸው ግን የነበራቸው አቀራረብ እጅግ የሚደነቅ ነበር። በዚህም ዋና አሰልጣኙ ያሬድ ገመቹ የተጫዋቾቻቸውን የማሸነፍ ስነልቦና ከማነሳሳት ባሻገር የመረጡት አሸናፊ ያደረጋቸው አጨዋወት ምርጥ ቡድናችንን እንዲመሩ አስችሏቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ሰዒድ ሀብታሙ – አዳማ ከተማ
አስቻለው ታመነ – መቻል
በረከት ወልደዮሐንስ – ሀዲያ ሆሳዕና
ሀይደር ሸረፋ – ኢትዮጵያ መድን
አቡበከር ሻሚል – አዳማ ከተማ
ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – ሻሸመኔ ከተማ
ኢዮብ ገብረማርያም – ሻሸመኔ ከተማ
ጄሮም ፍሊፕ – ኢትዮጵያ መድን