የዴንማርኩን ቡድን በማሰልጠን ላይ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ማነው ?

ክለቡን ከወራጅነት ለማዳን እየታገለ የሚገኘው ኢትዮጵያዊው የቀድሞ መምህር…


በተለያዩ የሕይወት አጋጣሚዎች ወደ አውሮፓ ያቀኑ እንዲሁም ከኢትዮጵያዊያን ቤተሰቦች የተገኙ ተጫዋቾች ቁጥራቸው በርካታ ነው። ወደ አሰልጣኝነት ገብተው በሞያው የገፉ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ግን አናሳ ነው። ቀደም ብለን የእስራኤሉን ታላቅ ክለብ በማሰልጠን ላይ የሚገኘው መሳይ ደጉን የተመለከቱ መረጃዎችና ዜናዎች ወደ እናንተ ማቅረባችን ይታወሳል፤ እነሆ ለዛሬ ደሞ ከወራት በፊት በዴንማርክ ሁለተኛ ዲቪዝዮን የሚሳተፈውን Fa 2000 ( Frederiksberg Alliancen 2000) ለማሰልጠን ተስማምቶ ክለቡን ከወራጅነት ለማዳን እየታገለ የሚገኘውን ወጣት አሰልጣኝ ልናስተዋውቃችሁ ወደናል።

ስሙ ሰመረ ኃይሌ ይባላል፤ ለአስራ ሦስት ዓመታት በቆየው የእግር ኳስ ሕይወቱ ለዴንማርኩ ታላቅ ክለብ FC Nordsjaellandን ጨምሮ ለስምንት ክለቦች ተጫውቷል። ከክለብ እግር ኳስ በተጨማሪም ለዴንማርክ ከአስራ ዘጠኝና ከሀያ ዓመት በታች ብሄራዊ ቡድኖች የተጫወተው ይህ አማካይ በአፍላ ዕድሜው ያሳየው ድንቅ ብቃት ከወቅቱ ምርጥ ተጫዋቾች ተርታ ቢያስመድበውም የገጠመው ተደጋጋሚ ጉዳት የእግር ኳስ ሕይወቱ ላይ ጫና ከማሳደር አልፎ  በጊዜ ጫማውን እንዲሰቅል አስገድዶታል።

በታዳጊነት ጊዜው ብዙ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው ብቃቱን አምኖ ሩቅ ያለመው ሰመረ ጉዳቶች ያጀቡት የእግር ኳስ ሕይወቱን ገና በሰላሣ ዓመቱ ለማገባደድ ቢወስንም ከዘርፉ ግን አልራቀም። ይልቁንስ ጊዜ ሳያባክን ወደ ስልጠናው ዓለም በመግባት አራት የታዲጊ ቡድኖች አሰልጥኗል። በታዳጊ ክለቦች የአሰልጣኝነት ቆይታው ጎን ለጎል የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህር በመሆን የሰራው ይህ ወጣት አሰልጣኝ በወቅቱ የ ‘Akademisk Boldklub’ ታዳጊ ቡድንን የውድድሩ አሸናፊ አድርጎ አሳዳጊ ክለቡን ክሷል። እናት ክለቡን ለድል ካበቃ በኋላም የትውልድ ከተማው ክለብ የሆነውን Herlev IF ወደ ሦስተኛው የሊግ እርከን በማሳደግ አጀማመሩን በሌላ ድል ለማጀብ በቅቷል።


በተለያዩ የታዳጊ ክለቦች ውጤታማ ጊዜ ማሳለፉ እንዲሁም በተጫዋችነት ጊዜው ያካበተው ልምድ በትልቅ ደረጃ እንዲታጭ የረዳው ሰመረ የ’Fa 2000′ ታዳጊ ቡድን ካሰለጠነ በኋላ የዋናው ቡድን የአሰልጣኝ ቡድን ለመቀላቀል ጊዜ አልፈጀበትም። አሁን ደግሞ ክለቡ ዋና አሰልጣኝኙ jonas Hjortshöj ማሰናበቱን ተከትሎ ቡድኑ ከመውረድ እንዲታደግ የዋና አሰልጣኝነት ቦታውን ተረክቦ ክለቡን ለማትረፍ እየታገለ ይገኛል።