የአሰልጣኞች አሰተያየት | ባህር ዳር ከተማ 2-1 ወልቂጤ ከተማ


“በዚህ ሰዓት ውጤቱ ነው ለእኛ ትልቅ ጉልበት” አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው

“ባለቀ ሰዓት በተፈጠረው እና በተሻረው ጎል ላይ ነው ጥያቄው እንጂ ሌላ ምንም የተለየ ነገር የለም” አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት

በ19ኛ ሳምንት ተስተካካይ መርሐግብር ባህርዳር ከተማ በቸርነት ጉግሳ የፍጹም ቅጣት ምት ጎሎች ወልቂጤ ከተማን 2ለ1 ካሸነፈበት ጨዋታ መቋጫ በኋላ የሁለቱም ቡድን አሰልጣኞች ለሶከር ኢትዮጵያ የድኅረ ጨዋታ አስተያየት ሰጥተዋል

አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምሕረት – ወልቂጤ ከተማ

ሰለ ጨዋታው…

“ጥሩ ጨዋታ ነበር ፣ ከቻልን ማሸነፍ ካለዚያ ደግሞ አንድ ነጥብ ይዞ ለመሄድ ነበር ተነጋግረን የመጣነው ግን ባለቀ ሰዓት ሆኖ አልተሳካልንም። ከመጀመሪያው ጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ የነበረው የቡድኑ መንፈስ በጣም አሪፍ ነው ጥሩ ነበር።”


በመጀመሪያው አጋማሽ ከነበራቸው ብልጫ አንፃር የተገኙ ዕድሎችን ያለ መጠቀም ውጤቱ ላይ ስለፈጠረው ተፅዕኖ….

“አለመጠቀማችን ውጤቱ ላይ ተፅዕኖ አይደለም ፣ እኛ ጋር ጉጉቱም አለ አሁን ካለንበትም ለመውጣት ችኮላ እና መጣደፎች ናቸው እንጂ ያሉት ጎሎች ቢገቡ አድቫንቴጆቹ የተሻሉ ይሆናሉ። አላማግባታችን በአጋጣሚ እነርሱ ፔናሊቲ አግኝተው አግብተውብናል ከዛ በኋላ ግን ለማግባት የሄድንባቸው መንገዶች ጥሩ ሆኖ አግብተን አቻ ሆነናል እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ጥረት እያደረግን ነበር ጎል አግብተን ተሽሯል ፣ አላወቅኩም መሻሩ ግን ተጫዋቾች ጋር ያለው መንፈስ ከጨዋታ ውጪ አይደለንም ነው እስከ መጨረሻው ሰዓት ድረስ ለማግባት እንቅስቃሴዎቻችን በጠቅላላ በጣም ጥሩ ነበሩ ቀድመን ብናገባ የተሻለ አድቫንቴጅ ይኖረን ነበር ብዬ አስባለሁ።”

ስለ ድሬዳዋ ቆይታቸው…

“ከሞላ ጎደል ጥሩ ነው። እንደ ቡድን የተንቀሳቀስናቸው እንቅስቃሴዎች በጣም ጥሩ ናቸው። የምንፈልጋቸውን ነገሮች ግን ከግብ አላደረስንም አሁን ካለንበት ለመውጣት ማሸነፍ ይጠበቅብናል ፣ ቀጣይ ቡድናችን ላይ ሲታይ የቆየው የአጥቂ ክፍተት ነው  ተጫዋቾች አሉን እነርሱን እንጠቀማለን ቀጣይ ብዬ አስባለሁ”።

ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በዳኝነቱ ላይ ስለነበረው ጥያቄ …

“ባለቀ ሰዓት በተፈጠረው እና በተሻረው ጎል ላይ ነው ጥያቄው እንጂ ሌላ ምንም የተለየ ነገር የለም ፣ ለምን እንደተሻረ የሁላችንም ጥያቄ ቢሆንም ዳኞች ግን ያዩት ነገር ይኖራል ግን ለማረጋገጫ ማረጋገጫ በዚህ ሰዓት የለንም እና ከመቀበል ውጪ አማራጭ የለንም”።

አሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው – ባህር ዳር ከተማ

ስለ ጨዋታው…

“ጨዋታው በጣም ከባድ ነው ፣ ወልቂጤ እጅግ ጠንካራ ክለብ ነው እጅግ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች ያሉበት ጨዋታን አንብበው ተረድተው መጫወት የሚችሉ እንደገናም ደግሞ ጨዋታን አቅልለው የሚጫወቱ ተጫዋቾች ያሉበት ቡድን ነው ካሉበት ደረጃም አኳያ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ጨዋታ ትንሽ ፈታኝ ነው ይህንን ቀድመንም ገምተን ነበር ፣ ነገር ግን ባሰብነው መንገድ በተለይ በመጀመሪያው አርባ አምስት ጨዋታው ላይ ጎል አግኝተን እንወጣለን የሚል ሀሳብ ነበረን ያ አልተሳካም። እንደ አጠቃላይ ያገኘነው ውጤት ተገቢ ነው ብዬ አስባለሁ ለተጫዋቾቻችንም አስተማሪ የሆነ ነገር ነው። ታስታውስ ከነበረ ከጊዮርጊስ ጋር በነበረን ጨዋታ በጭማሪ ሰዓት ነው ሚስ ያደረግነው ዛሬ ደግሞ በጭማሪ ሰዓት ውጤት አግኝተን የወጣንበት እና በየትኛውም ሰዓት እስከ መጨረሻው ድረስ ትኩረታቸውን ሳይስቱ መጫወት ይኖርባቸዋል። የዳኛው ፊሽካ እስኪጠናቀቅ ድረስ የሚችሉትን ማድረግ እንዳለባቸው ትልቅ ትምህርት ወስደውበታል ብዬ አስባለሁ ተጫዋቾቻችን እንደ አጠቃላይ ጥሩ ጨዋታ ነበር”።


በመጀመሪያው አጋማሽ ቡድኑ የነበረበት መቀዛቀዝ ከምን አንፃር የተፈጠረ ነው ….

“አጀማመራችን ምቾት የሚሰጥ አልነበረም ፣ ቀዝቃዛ ነበር ከቡድን ይልቅ የግል እንቅስቃሴዎች ይታዩ ነበር ፣ ምን አልባት ለጨዋታው የሰጡት ግምት ምን እንደሆነ ማወቅ አልቻልኩም። መልበሻ ክፍል ውስጥ ግን ፈታኝ የሆነ ጨዋታ እንደሚጠብቀን ተነጋግረን ነው የገባነው እና ሁለተኛው አርባ አምስት ላይ ያንን በተወሰነ ለመቅረፍ ሞክረናል። ትንሽ ቻርጅም የበዛበት ጨዋታ ነበር እንደ አጠቃላይ ግን በዚህ ሰዓት ውጤቱ ነው ለእኛ ትልቅ ጉልበት የሚሆን ተከታታይ ጨዋታዎችን ነጥብ ተጋርተን የወጣንበት ነበር እና ወደ መሪው ለመጠጋት እጅግ አስፈላጊ ውጤት ነው። ያም ይመስለኛል ጫና ውስጥ ናቸው ተጫዋቾች ውስጣቸው ማሳካት የሚፈልጉት እንደ ቡድን ማሳካት የምንፈልገው ነገር አለ ይሄ ፕሬዠር ውስጥ ከቷቸዋል ብዬ አስባለሁ።”

ከዚህ በፊት በነበረው ጨዋታ ፍፁም ቅጣት ምት አምክኖ ዛሬ ግን የተገኙትን ስላስቆጠረው ቸርነት ጉግሳ …

“የክለቡ የመጀመሪያ መቺ ያሬድ ነው። ያሬድ በሜዳው ላይ የለም ስለዚህ ከያሬድ ቀጥሎ ቸርነት እንዲመታ ነው የተመረጠው። ቸርነት አቅም ፣ ክላስ ያለው ተጫዋች ነው ምንአልባት በሀገራችን ኮሪደር ላይ እንደዚህ ዓይነት ተጫዋች ብቸኛው ነው ማለት ይቻላል አቅም አለው በቀደምም በረኛውን የት ሰዶት እንዴት እንደወጣ አይተኸዋል ፣ ለማመን የሚያስቸግር ኳስ ነው የወጣው እንጂ የአቅም ውስንነት ነው ብዬ አላስብም። ከምንም በላይ ደግሞ የናሽናል ቡድን ተጫዋቾች ነው የአጭር ጊዜ ልምዱም በራስ መተማመኑም ከፍ ያለ ተጫዋች ነው እና በዕርግጠኝነት ነበር ዛሬም ኳሶችን ይጨርሳል ብለን ያልነው እና በእግር ኳስ ውስጥ ያጋጥማል የባለፈው ዓይነት ግን ዛሬም ነገም እርሱን ነው የምንጠቀመው ፣ ያሬድ ወደ ሜዳ እስኪመለስ ድረስ ስለዚህ የተሻለ ጎል አስቆጥሯል እርሱም ደግሞ እየሄደበት ላለው በራስ መተማመን ከፍ ያደርግለታል ብዬ አስባለሁ።”

ስለ ድሬዳዋ ቆይታቸው…

“በድሬዳዋ ምቹ የሆነ የመጫወቻ ሜዳ ላዘጋጁልን የከተማው አስተዳደር እና ክቡር ከንቲባ ፤ ከነ ሕዝቡ ትልቅ ምስጋና አለኝ።”