ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አዲስ ከተማ እና ወሎ ኮምቦልቻ ማንሠራራታቸውን ቀጥለዋል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ “ለ” የ21ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ተከናውነው አዲስ ከተማ ተከታታይ ሦስተኛ ድሉን ሲያስመዘግብ ወሎ ኮምቦልቻ ከወራጅ ቀጠናው የወጣበትን ሦስት ነጥብ አሳክቷል።

በዕለቱ የመጀመርያ ጨዋታ አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ግርጌ ላይ የሚገኘው ካፋ ቡናን 4-0 አሸንፏል። የእንቅስቃሴ የበላይነት ወስደው የተጫወቱት አዲስ ከተማዎች የመጀመርያ ጎላቸውን ያገኙት በ18ኛው ደቂቃ ሲሆን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በሚያመሩበት ወቅት የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣት ምት በረከት አምባዬ በቀጥታ መትቶ በማስቆጠር መሪ አድርጓል።


በጎሉ ይበልጥ የተነቃቁት አዲስ ከተማዎች ከአራት ደቂቃ በኋላ ሁለተኛውን አክለዋል። ቅዱስ ተስፋዬ በመስመር በኩል ከቦጃ ጋር በአንድ ሁለት ቅብብል ይዘው የሄዱትን ኳስ ቅዱስ ወደ ጎልነት ለውጦ ልዩነቱን አስፍቷል።

በጨዋታው ብልጫ የተወሰደባቸው ካፋዎች ይባሱኑ በ28ኛው ደቂቃ ላይ ግብ ጠባቂያቸውን አጥተዋል። ጳውሎስ ከንቲባ የተሻገረውን ኳስ ቅዱስ ተስፋዬ ጋር ለመጠቀም ባደረገው ጥረት የካፋው ግብ ጠባቂ በቃሉ አሥራት ከግብ ክልሉ ውጪ ኳስ በእጅ በመንካቱ በቀይ ካርድ ከሜዳ ወጥቷል።

ደካማ እንቅስቃሴ ያደረጉት ካፋዎች በመጀመርያው አጋማሽ እምብዛም ወደ ተጋጣሚ የጎል ክልል ማምራት ያልቻሉ ሲሆን 42ኛው ደቂቃ ላይ ዮናታን ከበደ ሞክሮ ግብ ጠባቂ ካዳነበት ሙከራ ውጪ የሚጠቀስ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

ከዕረፍት መልስ ልክ እንደ መጀመሪያው አጋማሽ የበላይነት ማሳየታቸውን የቀጠሉት አዲስ ከተማዎች ብዙም ሳይቆዩ ተጨማሪ ጎል አስቆጥረዋል። በ52ኛው ደቂቃ ቅዱስ ተስፋዬ ከፍፁም እንድሪያስ የተቀበለውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ልዩነቱን ወደ ሦሰት አስፍቷል። በጭማሪ ደቂቃ ላይ ደግሞ ተቀይሮ የገባው ላመስግነው አበራ ከተካልኝ የተመቻቸለትን ኳስ አስቆጥሮ ጨዋታው በአዲስ ከተማ 4-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በሳምንቱ የመጨረሻ ጨዋታ ወሎ ኮምቦልቻ ደሴ ከተማን 2-1 አሸንፎ ከወራጅ ቀጠናው በመውጣት ደረጃውን አሻሽሏል።

በመጀመሪያው አጋማሽ ደሴዎች በኳስ ቁጥጥር የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ኮምቦልቻዎች ደግሞ ወደ ግብ በፍጥነት በመድረስ እና ዕድሎች በመፍጠር የተሻሉ ነበሩ። በዚህም በ28ኛው እና 31ኛው ደቂቃዎች ከመስመር በሚሻገሩ ኳሶች ጥሩ ዕድል ፈጥረው ነበር። በ33ኛው ደቂቃ ላይም ማኑሄ ጌታቸው ቢላል ገመዳ ያመቻቸለትን ኳስ በአግባቡ ተጠቅሞ ኮምቦልቻን ቀዳሚ አድርጓል።

ከጎሉ በኋላ በፍጥነት ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን ጎል ለማግኘት ጥረት ያደረጉት ደሴዎች ሰምሮላቸው ከስድስት ደቂቃዎች በኋላ በ39ኛው ዝናው ዘላለም ከቅጣት ምት የተሻማውን ኳስ በመግጨት ደሴን አቻ ማድረግ ችሏል።

ከዕረፍት መልስ ኮምቦልቻዎች በድጋሚ መሪ ለመሆን ደቂቃ አልፈጀባቸውም። አጋማሹ እንደተጀመረ ወደ ተጋጣሚ ክልል ይዘው በመሄድ በጨዋታው ጥሩ የተንቀሳቀሰው ቢላል ገመዳ ያቀበለውን ኳስ ማኑሄ ጌታቸው ለራሱም ለቡድኑም ሁለተኛ ጎል አድርጎታል።

ደሴዎች ከጎሉ በኋላ ጫና ፈጥረው በመጫወት ጎል ለማስቆጠር ሙከራዎች ያደረጉ ሲሆን 68ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋ ደርቤ መትቶ ግብ ጠባቂ ሲመልስበት ሙሉጌታ ካሳሁን አግኝቶ ቢመታም ወደ ላይ የወጣበት እንዲሁም 80ኛው ደቂቃ አቡሽ ከመሀል የተላከለትን ኳስ ሞክሮ ወደ ውጪ የወጣበት የሚጠቀሱ ሙከራዎች ነበሩ። ሆኖም መሪነታቸውን ለማስጠበቅ በጥንቃቄ የተጫወቱት ወሎ ኮምቦልቻዎች ተሳክቶላቸው ጨዋታውን 2-1 ማሸነፍ ችለዋል።