የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ | የ25ኛ ሳምንት ምርጥ 11

በርካታ ተጫዋቾች ጎልተው በወጡበት የጨዋታ ሳምንት በአንጻራዊነት ይህንን ምርጥ ቡድን ሠርተናል።

አደራደር 4-3-3

ግብ ጠባቂ

አቡበከር ኑራ – ኢትዮጵያ መድን

አበቡበከር ኑራ በርከት ላሉ ጊዜያት ከለመደው የመጀመርያ አሰላለፍ ወደ ተጠባባቂ ወንበር መውረዱ ቁጭት እና የበለጠ ለመሥራት መነሳሻ አድርጎ የተጠቀመበት መሆኑ ሰሞነኛው ድንቅ አቋሙ ምስክር ነው። ኢትዮጵያ መድን ድሬዳዋ ከተማን 5-0 በረመረመበት ጨዋታ አቡበከር ድርሻው ከፍያ ያለ ነበር። የተደረጉ ሙከራዎችን ከማክሸፍ በተጨማሪ ባለፉት በተከታታይ ሦስት ጨዋታዎች ላይ የግብ መረቡን ሳያስደፍር የወጣበት መንገድ ተደምሮ በምርጥ ስብስባችን ልናካትተው ወደናል።

ተከላካዮች

በፍቃዱ ዓለማየሁ -ኢትዮጵያ ቡና

በዘንድሮ የሊጉ ውድድር ክስተት ሆኖ ብቅ ያለው  የወደፊት ተስፈኛው በፍቃዱ ዓለማየሁ ስኬታማ ዓመታትን እያሳለፈ ይገኛል። በተስፋ ቡድን ከሚጫወትበት የአጥቂ ቦታ ፍፁማዊ ለውጥ በማድረግ የቡናማዎቹን የግራ መስመር ተከላካይ ቦታን በተገቢው መንገድ እየመራ የሚገኘው በፍቃዱ ሻሸመኔን ሲረቱ ቡድኑን ወደ ጨዋታ የመለሰች ጎል እንዲሁም ለራሱ የሊጉን የመጀመሪያ ጎል ከማስቆጠሩ በተጓዳኝ ቦታውን በአግባቡ በመቆጣጠር ቡድኑ በመጨረሻ ደቂቃ ወሳኝ ሦስት ነጥብ እንዲያገኝ በማጥቃቱ በኩል የነበረው አበርክቶ እንድንመርጠው አድርጎናል።

ካሌብ አማንክዋህ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

የቡድኑ ወሳኝ ተጫዋች መሆኑን በየጨዋታዎቹ በተገቢው ሁኔታ እያሳየ ያለው ካሌብ ቡድኑ
በጨዋታው ግብ ሳያስተናግድ እንዲወጣ ማድረግ ችሏል። ምንም እንኳን በርከት ያሉ ጥቃቶች በዲቻዎች በኩል ባይሰነዘርም በንቃት የመከላከል ወረዳውን ከመቆጣጠር ባለፈ ወደ ፊት ወጣ ብሎ በጥሩ ጊዜ አጠባበቅ ጥቃቶችን ከጅምሩ ሲያቋርጥ የነበረበት አኳኋን ግሩም ነበር። በተጨማሪም ለጎሎች መነሻ ሲሆን የነበረበት እጅግ አስፈላጊ እንቅስቃሴ ተመራጭ አድርጎታል።

ፍቅሩ ዓለማየሁ – አዳማ ከተማ

አዳማ ከተማ በብዙ ከሜዳ ውጭ ባሉ ውስብስብ ችግሮች በማለፍ ስኬታማ ዓመት ቡድኑ እንዲያሳልፍ ካስቻሉ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ፍቅሩ ዓለማየሁ ነው። ለአሰልጣኝ ይታገሱ እንዳለ የመከላከል አደራጃጀት ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች በመጫወት ቁልፍ ሚና እየተወጣ ያለው ፍቅሩ ሲዳማ ቡናን በረቱበት ጨዋታ የመከላከል ቀጠናውን በጥሩ ሁኔታ ከመጠበቅ ባለፈ ለሁለተኛ ጎል መገኘት ቀጥተኛ ተሳትፎ ሲያደርግ ለመጀመርያውም ጎል የኳሱ መነሻ እርሱ በመሆኑ ምርጫ ውስጥ አካተነዋል።

ኤፍሬም ታምራት –  ኢትዮጵያ ንገድ ባንክ

የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በታሪክ የመጀመርያውን ዋንጫ ለማንሳት በሚያደርገው ግስጋሴ በግራ መስመር ተከላካዩ ኤፍሬም ታምራት አስተዋፆኦ እያደገ መጥቷል። አሰልጣኝ በፀሎት በቦታው ትክክለኛ ሰው ለማግኘት በተቸገሩበት ወቅት መፍትሔ ሆኖ ብቅ ያለላቸው ኤፍሬም ዋና ሥራውን የመከላከሉን ሂደት በአግባቡ እየተወጣ ሲገኝ ለጎሎች መነሻ እየሆነ መጥቷል። ቡድኑ ወላይታ ድቻ ላይ አምስት ጎሎች ሲያስቆጥር አንዱን በስሙ በማስቆጠር በሊጉ የመጀመርያውን ጎሉን አግኝቷል።

አማካዮች

መሐመድ አበራ –  ኢትዮጵያ መድን

የመስመር አጥቂው መሐመድ ቀድሞ በነበራቸው የሊጉ ክለቦች ያሳይ የነበረውን ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ እንዳያሳይ ጉዳት ቢፈትነውም አሁን ወደ ሙሉ ጤንነቱ በመመለስ ለቡድኑ ውጤታማ መሆን ድርሻ ከፍ እያለ መጥቷል።
ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በተደጋጋሚ ራሱን ነፃ አድርጎ ለመግባት ያልተቸገረው እና በአንድ ለአንድ ግንኙነት ወቅትም ስኬታማ የነበረው መሐመድ ለሁለተኛው የፍፁም ቅጣት ምት ጎል መገኘት ምክንያቱ እርሱ ነበር።

ኪቲካ ጅማ – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ንግድ ባንኮች ወላይታ ድቻን 5ለ0 ሲያሸንፉ የመስመር አጥቂው እንቅስቃሴ ግሩም ነበር። የቡድኑን ፈጣን የማጥቃት ሽግግር ሲያሳልጥ የነበረው ኪቲካ ከእንቅስቃሴው ባሻገር ለቡድኑ አንድ ጎል በስሙ ማስመዝገብ ሲችል ለአንድ ጎልም አመቻችቶ ማቀበል ችሏል።

ከነዓን ማርክነህ – መቻል

መቻሎች ከሁለት ጊዜ መመራት ተነስተው በብርቱ ፉክክር ሀዋሳ ከተማን 3ለ2 ሲያሸንፉ የከነዓን አበርክቶ እጅግ ላቅ ያለ ነበር። የመስመር አጥቂው ሁለት ጎሎችን በስሙ ማስመዝገብ ሲችል በዕረፍት የለሽ ጠንካራ እንቅስቃሴውም የተጋጣሚ የኋላ መስመር ላይ ከፍተኛ ጫና መፍጠር ችሏል።

አጥቂዎች

ፍጹም ጥላሁን – ባህር ዳር ከተማ

የጣና ሞገዶቹ በደረጃው ግርጌ ላይ የሚገኘውን ሀምበርቾን 2ለ0 ሲያሸንፉ የመስመር አጥቂው ፍጹም ጥላሁን ኮከብ ሆኖ ውሏል። ፍጹም በርካታ የግብ ዕድሎችን ከመፍጠሩ ባሻገር የቡድኑን ሁለት ጎሎችም ማስቆጠር ሲችል በተለይም ሁለተኛው ግሩም ጎል የተጫዋቹን ክህሎት ያሳየ ነበር።

ሳይመን ፒተር – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

ንግድ ባንኮች የጦና ንቦቹ ላይ አምስት ግቦችን አስቆጥረው ሲያሸንፉ የዩጋንዳዊው አጥቂ የማጥቃት እንቅስቃሴ አስደናቂ ነበር። ሳይመን ሁለት ጎሎችን አመቻችቶ በማቀበል ለአንድ ጎል ቁልፍ መነሻ የነበር ሲሆን በስሙም አንድ ጎል አስመዝግቧል።

አለን ካይዋ – ኢትዮጵያ መድን

ኢትዮጵያ መድኖች ድሬዳዋ ከተማን 5ለ0 አሸንፈው አምስተኛ ተከታታይ ድላቸውን ሲያስመዘግቡ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ ከሻሸመኔ ከተማ ጋር ተለያይቶ ወደ ቡድኑ የተቀላቀለው አጥቂ ብቃት ልዩ ነበር። አለን ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ ሀት-ትሪክ መሥራት መቻሉም በውጤታማነቱ ረገድ ያለ ተቀናቃኝ ተመራጭ አድርጎታል።

አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ – መቻል

መቻሎች ከሁለት ጊዜ መመራት ተነስተው ሀዋሳን 3ለ2 ሲያሸንፉ የተጫዋቾች እጅግ የጋለ የጨዋታ ስሜት የሚደንቅ ነበር። ሆኖም ተጫዋቾቹ አቅማቸውን አውጥተው በተረጋጋ አስተውሎ እንዲንቀሳቀሱ በማድረጉ በኩል የተሳካላቸው አሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ከአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ እና ከአሰልጣኝ ገብረመድኅን ኃይሌ ጋር ተፎካክረው ከተጋጣሚያቸው ፈታኝነት አንጻር እና ከሁለት ጊዜ መመራት ተነስተው በማሸነፋቸው ቅድሚያ ተሰጥቷቸው የሳምንቱ ምርጥ ቡድናችንን እንዲመሩ ተመርጠዋል።

ተጠባባቂዎች

ፖሉማ ፖጁ – ሀምበርቾ
ረጀብ ሚፍታህ – ባህር ዳር ከተማ
ምንተስኖት ከበደ – ሻሸመኔ ከተማ
ራምኬል ጀምስ – ኢትዮጵያ ቡና
ዓባይነህ ፊኖ – ባህር ዳር ከተማ
ባሲሩ ኦማር – ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
ሽመልስ በቀለ – መቻል
ብሩክ ሙሉጌታ – ኢትዮጵያ መድን
ጌታነህ ከበደ – ፋሲል ከነማ
ዓሊ ሱሌይማን – ሀዋሳ ከተማ