የዋልያዎቹ ተጋጣሚ ከሀገር ውስጥ ሊግ ውጪ ለሚጫወቱ 25 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርባለች

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቀጣይ ተጋጣሚ ከሀገር ውስጥ ሊግ ውጪ ለሚጫወቱ 25 ተጫዋቾች ጥሪ አስተላልፋለች።

ለ2026 የዓለም ዋንጫ ለማለፍ የአህጉራችን ሀገራት በተለያዩ ምድቦች ተከፋፍለው የማጣሪያ ፍልሚያዎችን እያደረጉ የሚገኝ ሲሆን ከሁለት ሳምንታት በኋላም የምድብ ሦስተኛ እና አራተኛ ጨዋታዎች በቀናት ልዩነት ይከወናሉ። የሀገራችን ኢትዮጵያ ቀጣይ ተጋጣሚ የሆነችው ጊኒ ቢሳዎም ከሳምንታት በፊት ፓርቱጋላዊውን አሠልጣኝ ልዊስ ቦዋ ሞርት የቡድኑ አሠልጣኝ አድርጋ የሾመች ሲሆን ከፊቷ ላለባት የኢትዮጵያ እና ግብፅ ጨዋታም ከሰዓታት በፊት ለ25 ተጫዋቾች ጥሪ አቅርባለች።

ሁለቱንም ወሳኝ ጨዋታዎች በሜዳዋ የምታደርገው ጊኒ ሦስት የግብ ዘብ፣ ሰባት ተከላካዮች፣ ስምንት አማካኞች እንዲሁም ሰባት አጥቂዎች የጠራች ሲሆን ከስብስቡም አንድም ተጫዋች ከሀገር ውስጥ ሊግ አለመመረጡ ታውቋል። በዚህም በስብስቡ የሚገኙ ተጫዋቾች ከስፔን፣ ከፈረንሳይ፣ ከቻይና፣ ከኩዌት፣ ከዴንማርክ፣ ከስዌዘርላንድ፣ ከፖላንድ፣ ከተርኪ፣ ከሳይፕረስ፣ ከአሜሪካ፣ ከሳውዲ አረቢያ፣ ከፓርቱጋል፣ ከእስራኤል፣ ከቤልጂየም፣ ከግሪክ እና ከግብፅ ሊጎች የተመረጡ እንደሆነ ተመላክቷል።

የ46 ዓመቱ ልዊስ ቦው ሞርት በምርጫቸው በፊሪንስ ደ ፖርቱጋል የሚጫወተው እና በስፖርቲንግ ልምምድ እየሰራ የሚገኘው ኤልቪስ ባልዴን ለመጀመሪያ ጊዜ ጥሪ ሲያቀርቡለት ከ2019 ጀምሮ ከብሔራዊ ቡድኑ ርቆ የነበረው የ27 ዓመቱ ሮማሪዮ ባልዴ ወደ ቡድኑ የተመለሰበት ጥሪ አቅርበውለታል።

የኢትዮጵያ እና ጊኒ ቢሳዎ ጨዋታ ግንቦት 29 የሚከናወን ይሆናል።