ለአንጋፋው ፊዝዮቴራፒስት ይስሐቅ የዕውቅና መርሐ ግብር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጠ

በኢትዮጵያ እግርኳስ ከ30 ዓመት በላይ በሙያው ለሰጠው አገልግሎት ሊመሰገን ይገባል በሚል የተዘጋጀውን የዕውቅና መርሐ ግብር አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል።

በሆሊደይ ሆቴል በተሰጠው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ በሀገር ቤት ከተዋቀረው ኮሚቴዎች መካከል የቀድሞ ተጫዋቾች እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ቡድን መሪ አዳነ ግርማ ፣ የቀድሞ ዳኛ የአልቢትር እና የኢትዮጵያ ዳኞች ኮሚቴ አባል የሆነችው ሊዲያ ታፈሰ ፣ ለስፖርቱ በማንኛውም መልኩ ቅርብ የሆኑት እና በኢትዮጵያ ቡና ደጋፊነታቸው የሚታወቁት አቶ የሱፍ መሐመድ እና አቶ ሄኖክ ብርሀኑ ጥሪ የተደረገላቸው የሚዲያ አባላት በቦታው ተገኝተዋል።

የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኮሚቴው አባላት እንደተናገሩት ከሆነ “ ሰዎች ለሰሩት መልካም ስራ በሕይወት እያሉ ሊደሰቱ ሊመሰገኑ ይገባል። በሚል መነሻነት አንጋፋው ፊዝዮቴራፒስት ይስሐቅ ሽፈራው ከ30 ዓመት በላይ ሙያውን ለሁሉም ስፖርተኛ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ህዝብ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይል በቅንነት ያገለገለ ታላቅ ባለሙያ ነው። ለዚህም ላበረከተው አስተዋፆኦ እናክብረው እናመስገነው በሚል ተነሳሽነት በሀገር ቤትም ከሀገር ውጭ በሚገኙ የቀድሞ ተጫዋቾች እና ግለሰቦች ፍቃደኝነት በተዋቀረ ኮሚቴ አማካኝነት ለሦስት ወር ያህል የቆየ ስራዎች ሲሰሩ ቆይቶ አሁን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እንደደረሱ ተናግረው ይህ የዕውቅና የምስጋና ፕሮግራም በይስሐቅ ብቻ የሚቆም እንደማይሆን እና በቀጣይ ለኢትዮጵያ ስፖርት ውለታ ለዋሉ ሰዎች በተመሳሳይ ዕውቅና መስጠት እንደሚቀጥል ተናግረዋል። በማስከተል በቦታው ከተገኙ የሚዲያ አካላት ለቀረቡ አጭር ጥያቄዎች ኮሚቴዎቹ ምላሽ ሰጥተዋል።

በዕውቅና ፕሮግራሙን ለማዘጋጀት በሚደረገው ስራ ውስጥ የመንግስት ወይም የሚመለከታቸው የስፖርት አባላት ድረሻ ተሳትፎ እንዴት ነበር ?

አዳነ ግርማ

“ይህንን ስራ ለመስራት ስንጀምር ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ዘር፣ ሀይማኖትን፣ ክለብን ሳይለይ በቅንነት ላገለገለ ሰውን እናክብር ብለን ስንነሳ መንግስት ሆነ ማንንም አካል አማክረን አይደለም። የሰራን ሰው እናክብር በሚል ነው የተነሳሳ ነው። ስለዚህ ማንም አካል አልተሳተፈበትም። የእኛን በጎ አለማ እና ሀሳብ የደገፈ ሁሉ የተሳተፈበት ፕሮግራም ነው። እንደ ክብር እንግዳነት የሚመለከታቸውን ባለ ድርሻ አካላትን ጋብዘናል። በቀጣይ ይህ ተግባር በይስሐቅ ብቻ አይቆም በስፖርቱ ብዙ ሰርተው ያለፉ ሰዎች እንዲመሰገኑ እናደርጋለን። ዋናው ዓላማችን በስፖርቱ ዙርያ ማክበር፣ መመሰጋገን እንዲለመድ ማድግ ነው።”

በሦስት ወራት ጊዜ ውስጥ ምንም ስራዎች ስታከናውኑ ቆያቹ ? ምን ያህልስ ተሳክቶላቹኋል ?

አቶ የሱፍ መሐመድ

“ምን ያህል ተሳክቶላቹኋል ለተባልነው ለይስሐቅን ለማመስገን አቅደነው ከተነሳንበት ዕቅድ አንፃር ይመጥነዋል ብለን ካሰብነው መጠን ከመቶ ፕርሰንት በላይ ተሳክቶልናል። በሦስት ወር ውስጥ በርካት ስራዎች ተሰርተዋል። ለይስሐቅ ከሚደረገው የዕውቅና ዝግጅት ባለፈ የቀደሞ ተጫዋቾችን የማቀራረብ ስራዎች ተሰርቷል። ከዚህም ባለፈ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የሚገኙ ሰዎችን አንድ አድርጎ ለበጎ አላማ እንዲሰባሰቡ ማድረጉ ሌላው ትልቅ ስራ ነው። ኮሚቴው በቦታው እንዲገለፅ ስለፈለገ ነው ትልቅ ሰርፕራይዝ ጠብቁ። ለይስሐቅ ይመጥናል ብለን ያሰብነውን በሐሙሱ ዝግጅት ላይ የሚሸለም ይሆናል። በመንግስት አካላት በኩል ደብዳቤ ይዘን አልሄድንም። ያው ይታወቃል ብለን ስላሰብን ሆኖም ከስፖርት ቤተሰቡ በርካታ እገዛዎች አድርገዋል። የዛኑ ያህል ደግሞ ለይስሐቅ ቅርብ ናቸው ብለን ያሰብናቸው ግለሰቦች ጋር በደብዳቤ ጠይቀናቸው ያላገዙን ደግሞ አሉ። ሐሙስ ያገዙንን ሰዎች ይፋ እናደርጋለን። በአጠቃላይ ብዙዎች በከፍተኛ ጉጉት የሚጠበቅ ፕሮግራም እንደሚሆን እናስባለን።”

ሊዲያ ታፈሰ

“ይስሐቅን ለማክበር የተደረገው ርብርብ በጣም አስገራሚ ነው። በተለይ የቀድሞ ተጫዋቾች ያሳዩት ተሳትፎ እጅግ አስደሳች ነበር። በተዘጋጀው የሚዲያ ፕላት ፎርም እስከ ሌሊት ስምንት ሰዓት ድረስ ውይይት እየተደረገ በጣም የሚገርሙ ሀሳቦች እየተነሱ ብዙ የተለፋበት መስዋዕትነት የከፈሉበት ዝግጅት ነው። እንዲያውም አሁን ስሙ የማይጠቀስ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖር ቀድሞ የቅዱስ ጊዮርጊስ ለብሔራዊ ቡድን ተጫዋች “ዛሬ ቆሜ የምሄደው ይስሐቅ አክሞኝ በመዳኔ ነው የኔ ህይወት ይስሐቅ ነው ”በማለት የመጀመሪያውን ገንዘብ በመለገስ ስራው የተጀመረው። ይስሐቅ የሁሉ መዳኛ፣ ለሁሉ ባለውለታ፣ እጁ መድሀኒት የሆነ ሰው ነው። ይሄ ነው ሁሉንም ያግባባው። የይስሐቅ ፕሮግራም ሌላ መልካም ትሩፋቶችን ይዞልን ነው የመጣው።”

አቶ ሄኖክ ብርሀኑ

“ይስሐቅን ለማመስገን ስንቀሳቀስ አብዛኛዎቹ ሰዎች ይስሐቅ ምን ሆነ ብለው ይጠይቁ ነበር። ይስሐቅ የሆነው ምንም ነገር እንደሌለ ደጋግመን እንናገር ነበር። እኛ ሀገር የተለመደው ሰዎች ሲታመሙ፣ ሲቸገሩ ወይ ህይወታቸው ካለፈ በኋላ ነው እርዳታ እና ገንዘብ የሚጠየቀው። ይህን ለማስቀረት በህይወት እያለ ሰው ለሰራው መልካም ተግባር መመስገን አለበት ብለን ነው የተነሳነው። ይስሐቅ አሁንም በሙያው ያለ ጀግና ነው። በሐሙሱ ፕሮግራም ላይ በይስሐቅ የማመስገን ዝግጅት ላይ ተሳትፎ ያደረጉ አካላትን በጠቅላለ ጠርተናል። በዕለቱም ከሁለት መቶ እስከ ሁለት መቶ ሀምሳ ሰዎችን ጥሪ አድርገናል።”