የአጥቂ ስፍራ ተጫዋቹ ዛሬ ገና ዘግይቶ ወደ ቢሳው እያመራ ነው

ዋልያዎቹ በነገው ዕለት ከጊኒ ቢሳው ጋር ለሚያደርጉት ጨዋታ የቡድኑ አባላት ሰኞ ስፍራው ቢደርሱም አንድ ተጫዋች ግን ዘግይቶ ገና ዛሬ ወደ ስፋራው እያቀና እንደሆነ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

የዓለም ዋንጫ የአፍሪካ ዞን የቅድመ ማጣሪያ ጨዋታዎች ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ ሀገራት የሚደረጉ ሲሆን በምድብ አንድ የምትገኘው ሀገራችን ኢትዮጵያ በነገው ዕለት ከሜዳዋ ውጪ ቢሳው ላይ ከጊኒ ቢሳው ጋር ጨዋታዋን ታከናውናለች። ሰኞ ማለዳ ለጨዋታው ወደ ስፍራው ያመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ወደ 23 ተጫዋቾችን በመያዝ እንዳቀና የተገለፀ ቢሆንም ከወላይታ ድቻ የተመረጠው የፊት መስመር አጥቂው ቢኒያም ፍቅሬ ግን ለነገ ምሽቱ ጨዋታ ገና ዛሬ ወደ ስፍራው እያመራ እንዳለ ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።

ከቀናቶች በፊት በሀገር ቤት ዋልያዎቹ እያደረጉ በነበረው ዝግጅት የአንድ ቀን ልምምድ ላይ ከፓስፖርት ጉዳይ ጋር በተገናኘ ሳይገኝ ቀርቶ የነበረው ተጫዋቹ ለነገ ምሽቱ ጨዋታ ዛሬ ገና ዘግይቶ ወደ ስፍራው ማምራቱ አስገራሚ ሆኗል። በተለይ በአጥቂ መስመር ላይ የተጫዋቾች መሳሳት ያለበት ቡድኑ የባሰ ይህ ነገር ማጋጠሙ በነገው ጨዋታ ላይ ተፅዕኖ እንዳይፈጥርበት አስግቷል።