የሴቶች የዓለም ዋንጫ ወሳኝ ማጣሪያን ጨዋታ መዲናችን ታስተናግዳለች

የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የማጣርያ ወሳኝ ጨዋታ ነገ በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

በ2024 በዶሚኒካን ሪፐብሊክ አዘጋጅነት ለሚካሄደው የሴቶች ከ17 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የሚደረጉ የማጣርያ ጨዋታዎች የመጨረሻ ዙር ላይ ደርሰዋል። ይህን ተከትሎ አፍሪካን የሚወክሉ ሦስት ሀገራትን የሚለየው ወሳኝ ጨዋታዎች ዛሬ እና ነገ በሚደረጉ ጨዋታዎች የሚጀመሩ ይሆናል።

የመጨረሻ ማጣርያ ጨዋታቸውን ከሚያካሂዱት ሀገራት መካከል ቡሩንዲ እና ኬኒያ የሚያደርጉት የመጀመርያ ጨዋታ የቡሩንዲ ስታዲየም በካፍ ዕውቅና ያላገኘ በመሆኑ ጨዋታዋን በአዲስ አበባ እንዲደረግ ፍቃድ ጠይቀዋል። በዚህም መሠረት ካፍ ፍቃዱን መስጠቱን ተከትሎ ቡሩንዲ ባለሜዳ ጨዋታዋን ነገ በዘጠኝ ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም እንደምታደርግ አረጋግጠናል።

ሁለቱም ሀገራት ለጨዋታው አዲስ አበባ መግባታቸው ሲታወቅ የነገውን ጨዋታ ጊኒያውያን ዳኞች እንደሚመሩትም አውቀናል። በሌላ የማጣርያ ጨዋታዎች ዛምቢያ ከ ሞሮኮ እንዲሁም ላይቤሪያ ከ ናይጄሪያ ጋር የሚጫወቱ ይሆናል።