የነገውን የዋልያዎቹ ጨዋታ የሚመሩ አልቢትሮች ታውቀዋል

ነገ ምሽት 1 ሰዓት ጂቡቲ እና ኢትዮጵያ የሚያደርጉትን የጎረቤት ሀገራት ወሳኝ ፍልሚያ የሚመሩ አልቢትሮች ተለይተዋል።

የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ጨዋታዎች በተለያዩ የአህጉራችን ክፍሎች እየተከናወኑ የሚገኝ ሲሆን በምድብ 1 የምትገኘው ሀገራችን ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ሦስት ጨዋታዎችን አከናውና በድምሩ ሁለት ነጥብ በመያዝ የነገ ተጋጣሚዋን ጂቡቲ ብቻ በመብለጥ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። በነገው ዕለትም በሞሮኮ ኤልጀዲዳ ከተማ ኤል አብዲ ስታዲየም በምድብ አራተኛ ጨዋታ ጂቡቲን ትገጥማለች።

ይህንን የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት የሆኑትን ሀገራት ጨዋታም አራት ዩጋንዳዊ አልቢትሮች በዳኝነት እንደሚመሩት ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች። በዚህም ጨዋታውን በመሐል ዳኝነት ዓሊ ሳቢላ ቼለንጋት ሲመራው በረዳት ዳኝነት ደግሞ ሮናልድ ካቴንያ እና ሀኪም ሙሊንዳዋ እንዲሁም በአራተኛ ዳኝነት ዊልያም ኦሎያ ተሳትፎ ያደርጋሉ።

የጂቡቲ እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድኖች ጨዋታ ነገ ምሽት 1 ሰዓት የሚከናወን ይሆናል።