በምሽቱ ተጠባቂ መርሐግብር ምዓብ አናብስት እና የጣና ሞገዶቹ 1ለ1 ተለያይተዋል።
ባህር ዳር ከተማ ስሑል ሽረን ድል ያደረገው ቡድናቸውን ለውጥ ሳያደርጉበት ለዛሬው ጨዋታ ሲቀርቡ በመድን ሽንፈት አስተናግደው የነበሩት መቐለዎች ግን የአምስት ተጫዋቾችን ቅያሪ አድርገዋል። አንተነህ ገብረክርስቶስ ፣ ኪሩቤል ኃይሉ ፣ ቤንጃሚን ኮቱ ፣ አሸናፊ ሀፍቱ እና ክብሮም አፅብሀ አርፈው ሠለሞን ሀብቴ ፣ ሔኖክ አንጃው ፣ ያሬድ ከበደ ፣ ቦና ዓሊ እና ተመስገን በጅሮንድ ተተክተው ወደ ሜዳ ገብተዋል።
በኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ኤፍሬም ደበሌ እየተመራ በጀመረው የሁለቱ ቡድኖች የምሽቱ መርሐግብር በመጀመሪያዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ባህር ዳር ከተማዎች በኳስ ቁጥጥሩ ብልጫ ቢኖራቸውም ተጋጣሚያቸው ትተው የሚሄዱትን ክፍት ቦታ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ለመጠቀም የጣሩት መቐለ 70 እንደርታዎች 10ኛው ደቂቃ ላይ ጎል አስቆጥረዋል። በረጅሙ ወደ ቀኝ የተጣለን ኳስ ፀጋዬ አበራ በግንባር ሲገጭ ከጀርባው የተገኘው ብሩክ ሙሉጌታ በቀላሉ አግኝቶ ፔፔ ሰይዶ መረብ ላይ በማሳረፍ ቡድኑን ቀዳሚ አድርጓል።
ጨዋታው ሲቀጥል በይበልጥ ከአማካይ ክፍሉ ወደ መስመር ባዘነበለ የማጥቃት ሒደት በጥልቀት ለመንቀሳቀስ ጥረት ሲያደርጉ የተስተዋሉት ባህር ዳሮች በድግግሞሽ የመጨረሻው ሜዳ ላይ ደርሰው ያለቀላቸውን አጋጣሚዎች በተከታታይ ቢያገኙም ከአፈጻጸም አኳያ በእጅጉ ደካሞች ነበሩ። ከቀኝ መስመር በኩል የተሻማለትን ኳስ ፍፁም ዓለሙ በግንባር ጨርፎ ለጥቂት ያመለጥው አጋጣሚ በልዩነት በቡድኑ በኩል የምትነሳዋ ጥራት ያላት አጋጣሚ ነበረች። ጥንቃቄን መርጠው በመንቀሳቀስ የሚገኙ ኳሶችን በመልሶ ማጥቃት ይጫወቱ የነበሩት መቐለዎች አጋማሹን 1ለ0 እየመሩ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።
ከዕረፍት ጨዋታው ሲመለስ መጠነኛ መቀዛቀዞች በአጀማመሩ ብናይም ከደቂቃ ደቂቃ ግን የባህር ዳር ከተማ የእንቅስቃሴ የበላይነት እያየለ የመጣበት ሆኗል። የተጫዋች ቅያሪን ጭምር በማድረግ በአዲስ ጉልበት ሁለቱን መስመሮች በይበልጥ ተጠቅመው ወደ ሳጥን ቶሎ ቶሎ የሚደርሱት የአሰልጣኝ ደግአረገ ይግዛው ቡድን እንደነበራቸው የበላይነት ጥራት ያላቸውን ዕድሎች በመፍጠር ደረጃ ግን ውስንነት ታይቶባቸዋል። ለዚህም ማሳያ ቸርነት ከቀኝ በኩል በጥልቅ የጨዋታ መንገድ የማጥቃት ዕድሎችን በወጥነት ፈጥሮ ቢታይም በቀላሉ የሶፎኒያስ ሰይፈን መረብ መድፈር ላይ የስልነት ክፍተቶች የጎሉ ነበሩ።
የአብሥራ ተስፋዬ ከቀኝ መሬት ለመሬት ወደ ውስጥ አሻግሮ ቦና ዓሊ ተንሸራቶ ሁለተኛ ልትሆን ከምትችል አስቆጪ ሙከራ በስተቀር በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሞዓም አናብስቱ ሙሉ በሙሉ በባህር ዳር ለመበለጥ ተገደዋል።
የአቻ ውጤት ፍለጋቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ባህር ዳር ከተማዎች በመስመር ያደርጉ ከነበረው እንቅስቃሴ በተጨማሪ ከቆሙ እና ከተሻጋሪ ኳሶች በርካታ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር የቻሉ ቢሆንም የመቐለን የመከላከል አጥር ሰብሮ መግባቱ ላይ ግን ቀላል አልሆነላቸውም ይሁን እንጂ መደበኛው የጨዋታ ደቂቃ ተጠናቆ በተሰጡት ሰባት ጭማሪ ደቂቃዎች ውስጥ 90+1′ ላይ ቸርነት ጉግሳ ከቀኝ ወደ ውስጥ ያሻገራትን እና የግብ ዘቡ ሶፎኒያስ ሰይፈ የመለሳትን ኳስ ወንድወሰን በለጠ በማስቆጠር የጣና ሞገዶቹን በመጨረሻም 1ለ1 በማድረግ ጨዋታው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ ችሏል።