ሪፖርት | የመቻል እና ወልዋሎ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

ሪፖርት | የመቻል እና ወልዋሎ ጨዋታ ያለ ጎል ተጠናቋል

በብዙ መመዘኛዎች ደካማ በነበረው የዕለቱ ቀዳሚ መርሃግብር ያለግብ ተቋጭቷል።


ሁለቱም ቡድኖች በመጨረሻው የጨዋታ ሳምንት ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ 11 ስብስብ በተመሳሳይ የሁለት ተጫዋቾችን ለውጥ ሲያደርጉ መቻሎች ከድሬዳዋ ጋር ያለ ጎል ካጠናቀቁበት ጨዋታ ፊልሞን ገብረፃዲቅን በዮሐንስ መንግሥቱ ፣ አብዱ ሞታለባን በሽመልስ በቀለ የተኩ ሲሆን በአንፃሩ ከሲዳማ ቡና ጋር 1ለ1 አጠናቀው የነበሩት ወልዋሎች በበኩላቸው ሠለሞን ገመቹን በኪሩቤል ወንድሙ ፣ ጋዲሳ መብራቴን በሀብታሙ ንጉሴ ለውጠው ገብተዋል።

በኢንተርናሽናል ዳኛ ሀይለየሱስ ባዘዘው እየተመራ በጀመረው ጨዋታ በመጀመሪያዎቹ ሀያ ደቂቃዎች ውስጥ መቻሎች በይበልጥ ጫናን ፈጥረው የተንቀሳቀሱበት ነበር። ሦስቱን ዋነኛ የማጥቂያ መስመሮችን በተጠቀሱት ደቂቃዎች በስብጥር ተጠቅመው በድግግሞሽ በሳጥን ውስጥ ይገኙ የነበሩት መቻሎች በ2ኛው ደቂቃ ከማዕዘን ከተሻማ ኳስ ፍሪምፓንግ ገጭቶ የሰጠውን አቤል ነጋሽ በግንባር ገጭቶ በግቡ ቋሚ ብረት በተመለሰች አጋጣሚ ፈጣኗን ሙከራ ሰንዝረዋል።

በተጋጣሚያቸው የእንቅስቃሴ የበላይነት የተወሰደባቸው እና የሚያገኟቸውን ውስን ዕድሎች ረዘም ባሉ ኳሶች ለመጠቀም ጥረት ሲያደርጉ የታዩት ወልዋሎች በአንድ አጋጣሚ ዳዋ ሆቴሳ ከቅጣት ምት ካደረጋት ደካማ ሙከራ ውጪ በአጋማሹ ያደረጉት ሌላ ተጨማሪ ሙከራ አልነበረም።

በኳስ ቁጥጥር ረገድ ብልጫ የነበራቸው መቻሎች እንደነበራቸው ብልጫ ግልፅ አጋጣሚዎችን ማግኘት አልቻሉም። 19ኛው ደቂቃ ግሩም ሐጎስ ከቅጣት ምት እንዲሁም ከደቂቃዎች በኋላ ከማዕዘን የተነሳች ኳስን በመጨረሻም እግሩ ስር ያገኘው ሽመልስ በቀለ ካደረጋት ሙከራ መልስ አጋማሹ ጎልን ሳያስመለክተን ተገባዷል።

ከዕረፍት መልስ የተጫዋች ቅያሪን በማድረግ ወደ ሜዳ የተመለሱት ወልዋሎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በአንፃራዊነት በተወሰነ መልኩ የተሻለውን እንቅስቃሴ ያደረጉ ቢሆንም መቻሎች ኳስን በመቆጣጠር በድግግሞሽ ሳጥን ደርሶ አጋጣሚዎችን በመፍጠሩ ብልጫ ነበራቸው ይሁን እንጂ ቡድኑ እንደነበረው ብልጫ ጥራት ያለውን አጋጣሚ መፍጠሩ ከብዷቸው ተመልክተናል።

ጨዋታው ሊጠናቀቅ ወደ መጨረሻዎቹ አስራ አምስት ደቂቃዎች ከፍ ያለውን ግለት ቢያሳየንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ሳናይበት 0ለ0 ተጠናቋል።