ኢትዮጵያ መድንን ከ ድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው የጨዋታ ሳምንቱ የመዝጊያ መርሃግብር በመሐመድ አበራ ብቸኛ ግብ ኢትዮጵያ መድንን 1-0 አሸናፊ አድርጎ ተጠናቋል።
በኢዮብ ሰንደቁ
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት በወላይታ ድቻ 1-0 በሆነ ውጤት የተሸነፋት ኢትዮጵያ መድኖች ዋንጫ ቱት እና መስፍን ዋሼን በማሳረፍ በምትካቸው አዲስ ተስፋዬ እና አለን ካይዋ ወደ ሜዳ ሲገቡ ድሬዳዋ ከተማዎች መቻል ጋር ነጥብ ከተጋሩበት ጨዋታ አንድ ተጫዋች ብቻ ቀይረው መስዑድ መሐመድን በሱራፌል ጌታቸው በመተካት ጨዋታቸውን ጀምረዋል።
ምሽት 12 ሰዓት ሲል በአ.ሳ.ቴ.ዩ ስታዲየም የተጀመረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከጅማሬው አንስቶ እሰከ መጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂያ ሰዓት ድረስ ተቀዛቅዞ የቀጠለ እንዲሁም ለተመልካች ሳቢ እና ማራኪ ያልነበረ ጨዋታ ነበር።
ያለፈውን ጨዋታ ሽንፈታቸውን ለማካካስ ይበልጥ በማጥቃት ላይ አተኩረው የነበሩት ኢትዮጵያ መድኖች ከሀሳብ የዘለለ ይህ ነው ሚባል ሙከራ ማድረግ ሳይችሉ ቀርተዋል። በተቃራኒው መከላከልን ምርጫቸው ያደረጉት የምስራቅ ተወካዮች ድሬዳዋ ከተማዎች ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ከመከላከል ወደ ማጥቃቱ ሲሸጋገሩ ተመልክተናል።
ተቀዛቅዞ በቀጠለው ጨዋታ 22ኛው ደቂቃ ላይ በቻርለስ ሙሴጌ አማካኝነት ካየነው ደከም ያለ ሙከራ በስተቀር ምንም ዒላማውን የጠበቀ የኳስ መከራ ሳያስመለክተን የመጀመሪያው አጋማሽ ያለ ግብ ተጠናቋል።
ከዕረፍት መልስ በመጠኑም ቢሆን በኳስ ቁጥጥር እና እንቅስቃሴ ተሻሽለው የቀረቡት ሁለቱም ቡድኖች በማጥቃት ፍላጎቱ ረገድ ጎልተው የተንቀሳቀሱበት አጋማሽ ነበር በዚህም 66ኛው ደቂቃ ላይ ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በቅበብሎሽ መድረስ የቻሉ ሲሆን ሙኸዲን ሙሳ ሳጥን ውስጥ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ አስራት ቱንጆ ቢሞክረውም ለጥቂት በግቡ ቋሚ ወጥቶበታል።
ለ69 ያክል ደቂቃዎች ምንም ዓይነት ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት ኢትዮጵያ መድኖች በመጀመሪያ ሙከራቸው ኳስን ከመረብ ጋር ማገናኘት ችለዋል። በቀኝ መስመር በኩል ከበረከት ካሌብ መነሻውን ያደረገው የአየር ኳስ አቡበከር ሳኒ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረውን ኳስ ጥሩ አቋቋም ላይ ሁኖ ያገኘው አጥቂው መሐመድ አበራ ወደ ግብነት በመቀየር መድኖችን መሪ ማድረግ ችሏል።
የአቻነቱን ግብ ለማግኘት ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ድሬዎች 77ኛው ደቂቃ ላይ አስራት አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ሙኸዲን ሙሳን ቀይሮ የገባው ዮሐንስ የመታው ኳስ የግቡን አግዳሚ በመግጨት ለድሬዎች አስቆጪ ዕድል መሆን ችሏል። ድሬዳዋ ከተማዎች ከጎሉ መቆጠር በኋላ በቁጥር ብልጫ ወስደው አቻ ሚሆኑበትን ጎል ለማስቆጠር ጫና ፈጥረው መጫወት ቢችሉም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ ሲከላከሉ የነበሩትን መድኖች አጥር ማስከፈት ተስኗቸው ጨዋታውን በኢትዮጵያ መድን አሸናፊነት 1-0 ተጠናቋል።