ፍቅሩ ተፈራ ዳግም ፊቱን ወደ ህንድ አዙሯል

ኢትዮጵያዊው አጥቂ ፍቅሩ ተፈራ ዳግም ወደ ህንድ አምርቶ የእግርኳስ ህይወቱን እንደሚቀጥል ለደቡብ አፍሪካው ድረ-ገፅ Kickoff ገልጿል፡፡ ተጓዡ ፍቅሩ ለደቡብ አፍሪካው ክለብ ሃይላንድስ ፓርክ ለአጭር ወራት የተጫወተ ሲሆን ውሉን ከተጠናቀቀ በኃላ ከአብሳ ፕሪምየርሺፕ የወረደውን ክለብ ለቋል፡፡

የህንድ ሂሮ ሱፐር ሊግ የ2017/18 የውድድር ዘመን በህዳር ወር የሚጀምር ሲሆን የሁለት ግዜ ቻምፒዮን መሆን የቻለው ፍቅሩ በሊጉ ላይ የሚሳተፉ ክለቦች ፍላጎት ማሳየታቸውን ተከትሎ ወደ ህንድ መሄዱን እንደመጀመሪያ አማራጭ ይዞታል፡፡ “እየተመለከትኳቸው ያለሁት የተወሰኑ ምርጫዎች ህንድ ላይ አሉኝ፡፡ በህንድ ከዚህ ቀደም ተጫውቻለው ፤ ስለዚህም ሊጉ አይከብደኝም፡፡ አሁን ላይ ረዘም ያለ እና ትልቅ ሊግ ስለሚሆን እኔም እንደአዲስ ለመጀመር አዲስ ክለብ የምቀላቀል ይሆናል፡፡” ብሏል፡፡

ከኢትዮጵያ ውጪ ለ10 ዓመታት ያህል በ6 ሃገራት እግርኳስን መጫወት የቻለው ፍቅሩ በደቡብ አፍሪካ እግርኳስ ማህበር እየተሰጠ ያለው የካፍ ሲ የአሰልጣኝነት ኮርስ በመውሰድ ላይ ይገኛል፡፡

ተጫዋቹ ሃይላንድስ ፓርክን ከመቀላቀሉ አስቀድሞ በህንድ ሊግ ለሚወዳደረው መሃመዳን ክለብ ለመፈረም ከጫፍ ደርሶ ነበር፡፡ ፍቅሩ በህንድ ቆይታው ለአትሌቲኮ ደ ኮልካታ እና ቺናይ ክለቦች መጫወት የቻለ ሲሆን ከሁለቱም ክለቦች ጋር የሊጉን ዋንጫ ክብር ማሳካት ችሏል፡፡ ፍቅሩ በኮልካታው ክለብ አትሌቲኮ ደ ኮልካታ ቆይታው በመጀመሪያው የህንድ ሂሮ ሱፐር ሊግ ግብን ሙምባይ ሲቲ ላይ በማስቆጠር በታሪክ መዝገብ ላይ ሰፍሯል፡፡

የህንድ ሂሮ ሱፐር ሊግ ተሳታፊ ክለቦች ከ8 ወደ 10 ያደገ ሲሆን የውድድር ዘመኑ ጨዋታዎች ቁጥርም የሚጨምር ይሆናል፡፡ እግርኳስን በኢትዮጵያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ ፊንላንድ፣ ቬይትናም፣ ባንግላዴሽ እና  ህንድ የተጫወተው በራሪው ፍቅሩ አዲሱን ክለቡ በቅርብ ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *