የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የሴካፋ ዝግጅቱን ዛሬ ጀመረ 

በህዳር ወር መጨረሻ በአስር ሀገራት መካከል በሁለት ምድብ ተከፍሎ በኬንያ አሰተናጋጅነት የሚካሄደው የሴካፋ ዋንጫ ላይ ተሳታፊ የሚሆነው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ ቀን ዝግጅቱን ዛሬ ረፋድ ላይ በአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እየተመራ አድርጓል።

ባልተሟላ ትጥቅ ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ጥሪ ከተደረገላቸው 27 ተጨዋቾች መካከል በዛሬው ረፋድ ላይ ልምምድ 22 ተጨዋቾች የተገኙ ሲሆን ተስፋዬ አለባቸው እና ብሩክ ቀልቦሬ ከወልድያ ፣  ዮናስ ገረመው እና ኄኖክ አዱኛ ከጅማ አባጅፋር እንዲሁም አማኑኤል ገ/ሚካኤል ከመቐለ ከተማ ያልተገኙ ተጫዋቾች ናቸው። ከአሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ የአሰልጣኝ አባላት ውስጥ ም/አሰልጣኙ በለጠ ገ/ኪዳን በማሰልጠን ስራቸው ያልተገኙ መሆናቸውንም ለማወቅ ችለናል። በስም ስህተት የተጠራው በኃይሉ ተሻገር ሳይሆን ኃይሌ እሸቱ ሆኖ ዛሬ ልምምድ ላይ መገኘቱም አስገራሚ ክስተት ሆኗል።

አስቀድሞ አንዳንድ ክለቦች ካለባቸው ወሳኝ የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ አኳያ ተጫዋቾችን እንደማይልኩ ፍንጭ በሰጠነው መሰረት ምን አልባት ከዛሬ በኋላ የተፈጠረ አዲስ ነገር ከሌለ ወልድያ ፣ ጅማ አባጅፋር እና መቐለ ከተማ ተጨዋቾቻቸውን የማይልኩ ክለቦች ይሆናሉ ተብሏል። ጥሪ ተደረጎላቸው የተሰባሰቡ ተጫዋቾችም ክለባቸው በአራተኛ ሳምንት በሚኖረው ጨዋታ ወደ ክለባቸው በማምራት አገልግሎት ሊሰጡ እንደሚችል ሰምተናል።

ከአንድ ሰአት በላይ በቆየው የዛሬ ውሎ ቀለል ያለ እና ከኳስ ጋር መሰረት ያደረገ የቅንጅት ስራን ያካተተ ልምምድ ሲሰሩ በግማሽ ሜዳም እርስ በእርስ ተጫውተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ነገ የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ ተስተካካይ ጨዋታ ያለባቸው ሳምሶን ጥላሁን፣ መስኡድ መሀመድ (ከኢትዮዽያ ቡና) ፣ አዲስ ግደይ እና አበበ ጥላሁን (ከሲዳማ ቡና) ተነጥለው ሰውነት የሟሟቅ ሰርተው እረፍት ሲያደርጉ ተመልክተናል።

አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ ስለ ዝግጅታቸው ለጋዜጠኞች የሚከተለውን አስተያየት ሰጥተዋል።

ስለ ሴካፋ

” ወደ ውድድር የምናመራው ለተሳትፎ ሳይሆን የውድድሩ አሸናፊ ለመሆነው። ተጫዋቾቹም ታሪክ ይሰራሉ ብዬ አስባለው። የመጫወት ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው። ”

ስለተመረጡት ተጫዋቾች

” የሴካፋ ዋንጫ መኖሩ ተተኪ ተጫዋቾችን ልምድ ለመስጠት ይረዳናል። ባሉት ተጫዋቾችም ነኝ። ”

ስላልመጡት ተጫዋቾች

” የሦስት ክለብ ተጨዋቾች አልመጡም። ተጨዋቾቹ ፍቃደኛ ቢሆኑም የክለቦቹ አመራሮች ሊልኩ አልቻሉም። ከአመራሮቹ ጋር ተነጋግረን መግባባት ላይ ደርሰናል። ዛሬ ተጨዋቾቹ ይገባሉ ብለን እንጠብቃለን። ”

ከአንድ ክለብ በርካታ ተጫዋች አለመምረጥ

” ሊጉ እንዳይቋረጥ ከአንድ ክለብ ሁለት ተጫዋች መመረጡ የሚያሳድረው ተፅእኖ አለ። አስፍተን ጠንካራ ተጫዋቾች እንዳንመርጥ ቢያደርገንም የሀገሪቱ ትልቅ ውድድር መቋረጡ ጉዳት ያለው በመሆኑ ውድድሩ መቀጠሉ መልካም ነው።”

ስለ ፓስፖርት ችግሮች

” ከነገ ጀምሮ ፕሮግራሜ ይህ ነው። እነዚህ ተጫዋቾች ወደድንም ጠላንም የነገ ተስፋ ናቸው። ስለዚህ በፓስፖርት ችግር ምክንያት መቅረት የለባቸውም። የሁላችንም ርብርብ ያስፈልጋል”

የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን የመጀመርያ የምድብ ጨዋታውን ህዳር 25 ቀን 2010 ከቡርንዲ ጋር የሚያደርግ ይሆናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *