​ሪፖርት| ደደቢት ሲዳማ ቡና ላይ የግብ ናዳ ሲያወርድ ባለ ሐት-ትሪኩ አቤል ደምቆ ውሏል

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት መርሃ ግብር ዛሬ መካሄድ ሲጀምር አዲስ አበባ ስታድየም ላይ ሲዳማ ቡናን ያስተናገደው ደደቢት ከመመራት ተነስቶ በአቤል ያለው ሐት-ትሪክ በመታገዝ 5-2 በሆነ ውጤት በማሸነፍ ሊጉን መምራት ጀምሯል፡፡

በሴካፋ ውድድር ምክንያት ከቡድናቸው ተለይተው የነበሩት ተከላካዩ አበበ ጥላሁንና የመስመር አጥቂው አዲስ ግደይ በሲዳማ ቡና በኩል እንዲሁም አጥቂው አቤል ያለው በደደቢት በኩል ከብሔራዊ ቡድን መመለሳቸውን ተከትሎ ሁለቱም ቡድኖች ከሰሞኑ በተለየ ጠንካራ የሚባለውን የቡድን ስብስባቸውን ይዘው ነበር ጨዋታውን መጀመር የቻሉት፡፡

ደደቢቶች በተለይም በዘንድሮው የውድድር ዘመን ይጠቀሙበት ከነበረው የ4-2-3-1/4-4-2 ቅርፅ በተለየ ባልተለመደ መልኩ በ4-3-3 አሰላለፍ አቤል ያለውንና ሽመክት ጉግሳን ከጌታነህ ጋር ፊት መስመር ላይ በማጣመር ነበር ጨዋታውን የጀመሩት፡፡ ሶስት ተጨዋቾችን በቅጣት ያጡት ሲዳማ ቡናዎች በበኩላቸው አብዱለጢፍ መሀመድን ወደ ተጠባባቂ ወንበር በማውረድ ለአብይ በየነ እና ሀብታሙ ገዛኸኝ ቅድሚያ የመሰለፍ ዕድል ሰጥተዋል።

ከጨዋታው ጅማሮ አንስቶ ደደቢቶች በፈጣን የመስመር አጨዋወት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ ጫና መፍጠር ችለዋል፡፡ በ4ኛው ደቂቃ ላይ ሽመክት ከቀኝ መስመር ያሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ ጌታነህ ከበደ ግብ ማስቆጠር ቢችልም ጨዋታውን የመሩት ዳኛ ጌታነህ ኳሱን ሲቀበል ከጨዋታ ውጪ አቋቋም ላይ ነበር በሚል ሳያፀድቁት ቀርተዋል፡፡ በየአብስራ ተስፋዬ እና አቤል እንዳለ የመሀል ሜዳ እንቅስቃሴ ላይ ተመስርተው በተጋጣሚያቸው ላይ የበላይነት የወሰዱት ደደቢቶች እንደነበረባቸው ብልጫ ይህ ነው የሚባል የግብ እድል መፍጠር አልቻሉም ነበር።

በአንፃሩ በመጠኑም ቢሆን ወደ ኃላ በማፈግፈግ በመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ ለመጫወት ያሰቡ የሚመስሉት የነበሩት ሲዳማ ቡናዎች በሚያገኟቸው አጋጣሚዎች ወደፊት ሲሄዱ ወደ መሀል ሜዳው ከቀረበው የደደቢት የተከላካይ መስመር ጀርባ በመግባት የተሻለ አስፈሪነት ተላብሰው ታይተዋል። በተመሳሳይ እንቅስቃሴ የደደቢትን የጨዋታ ውጪ መረብ በማለፍ በግራ መስመር የተላከለትን ኳስ ይዞ የገባው አዲስ ግደይ 22ኛው ደቂቃ ላይ በግሩም ሁኔታ ያስቆጠራት ጎል ሲዳማዎች ጨዋታውን እንዲመሩ ዕድል የሰጠች ነበረች። ከግቧ መቆጠር በኃላ አቻ ለመሆን ከፍተኛ ጥረት ባደረጉት ደደቢቶች በኩል በተለይ ጌታነህ ከበደ ከሲዳማ ቡናዎች የግብ ክልል በቀጥታ ወደ ግብ የላካትን አስደናቂ ኳስ የሲዳማው ግብ ጠባቂ ፍቅሩ ወዲሳ በሚገርም ሁኔታ ሊያድንበት ችሏል፡፡ በዚህ መሀል አማካያቸው አቤል እንዳለን በጉዳት ያጡት ደደቢቶች አለምአንተ ካሳን ቀይረው በማስገባት ግብ የማግኘት ጥረታቸውን ቀጥለዋል። በዚህም የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል ጌታነህ ከበደ በሲዳማ ቡና ተከላካዮች አናት ያሳለፈለትን ኳስ ተጠቅሞ አቤል ያለው ከሴካፋ መልስ ባስቆጠራት የመጀመሪያ ጎል አማካይነት አቻ መሆን ችለዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ፈጣን የጨዋታ እንቅስቃሴ እና አምስት ግቦችን ያሳየን ሆኖ አልፏል። ከአምስቱ ግቦች አራቱን ያስቆጠሩት ግን ባለሜዳዎቹ ደደቢቶች ነበሩ።  ከመጀመሪያው በተሻለ ይበልጥ ጫና ፈጥረው መጫወት የቻሉት ደደቢቶች የነበራቸው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ወደ ግብ ዕድሎች መለውጥ ጀምሮ በ55ኛው እንዲሁም በ59ኛው ደቂቃ ላይ ደስታ ደሙ እና አቤል ያለው አከታትለው ባስቆጠሯቸው ጎሎች 3ለ1 መምራት ቻሉ። በዚህ ወቅት ጨዋታው ያበቃለት ቢመስልም  በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ጋናዊ የመስመር አጥቂ መሀመድ አብዱለቲፍ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ በግራው የሳጥን ጠርዝ ይዞ የገባውን ኳስ አክርሮ መቶ 66ኛው ደቂቃ ላይ በማስቆጠር የግብ ልዩነቱን አጥብቦ ለአሰልጣኝ አለማየሁ አባይነህ ቡድን ተስፋ መስጠት ቻለ። ይህ ግብ ሲቆጠር በነበረው እና በቀጣዮቹ ደቂቃዎችም ጭምር የደደቢት የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎች የመከላከል ተሳትፎ እየወረደ መምጣቱን ተከትሎ ሲዳማዎች ጫናቸው እጅግ እየበረታ ተደጋጋሚ የግብ ዕድሎችንም እየፈጠሩ ቢቆዩም የአቻነት ግብ ማስቆጠር ግን አልቻሉም። ይህን ክፍተታቸውን በቅያሪዎች ለማስተካከል ሲሞክሩ የታዩት ደደቢቶች የገቡበትን ጫና ለመቋቋም ከማፈግፈግ ይልቅ በተለይ በጌታነህ ከበደ አማካይነት አፀፋውን ለመመለስ ሲጥሩ ታይቷል። በመጨረሻም ተሳክቶላቸው በ83ተኛው እንዲሁም በ89ኛው ደቂቃ ላይ ኤፍሬም አሻሞና አቤል ያለው ባስቆጠሯቸው ግቦች 5ለ2 አሸንፈው መውጣት ችለዋል፡፡

አቤል ያለው ከሴካፋ መልስ በዛሬው ጨዋታ ሐት-ትሪክ መስራት ችሏል ፤ ይህም በዘንድሮው የውድድር ዘመን የ7 ሳምንት ጉዞ የሀዋሳው ዳዊት ፍቃዱ ወልዲያ ላይ ካስቆጠረው ቀጥሎ የተቆጠረ ሁለተኛ ሐት-ትሪክ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡ ጨዋታውም በሊጉ ባልተለመደ መልኩ ሰባት ግቦችን ያስተናገደ መሆኑ በስቴድየም የተገኘው ጥቂት ደጋፊ ዕድለኛ ሆኖ አሳልፏል። የዛሬውን ውጤትም ተከትሎ ደደቢት ከ7 ሳምንት ጨዋታዎች በኃላ በ13 ነጥብ ሊጉን መምራት ጀምሯል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ንጉሴ ደስታ- ደደቢት

“ቡድናችን በተለይ በመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ደካማ ነበር ነገርግን በአሁኑ ወቅት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻልን መጥተናል፡፡ቡድኑ እንደ ቡድን አጥቅቶ ለመጫወት ከጊዜ ወደ ጊዜ የተሻለ ጥረት እያደረግን እንገኛለን፡፡”

አለማየሁ አባይነህ – ሲዳማ ቡና

“ቡድናችን በክረምቱ የዝውውር መስኮት በርካታ ተጫዋቾች እንደመልቀቃችን እንደ አዲስ እየተገነባ ይገኛል ፤ በተጨማሪም በየጨዋታው የምናያቸው ካርዶች ዋጋ እያስከፈሉን ይገኛል”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *