​የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 7ኛ ሳምንት – የእሁድ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

ትላንትት ሁለት ጨዋታዎች የተስተናገዱበት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት ዛሬ በሚደረጉ አራት ጨዋታዎች ቀጥሎ ይውላል። በዓዲግራት ፣ ሶዶ ፣ አዳማ እና አዲስ አበባ የሚደረጉትን አራቱን ጨዋታዎች አስመልክተንም የሚከተሉትን ነጥቦች ልናነሳ ወደድን።

ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ መከላከያ

ጨዋታው የትናንቱን የደደቢት ድል ተከትሎ ወደ ሁለተኛነት ዝቅ ያለው ወልዋሎ ወደ መሪነት ለመመለስ የሚያደርገው ሲሆን መከላከያም ማሸነፍ ከቻለ ምን አልባትም ያለበትን የመጨረሻ ደረጃ ለማሻሻል የሚችል ይሆናል። የሁለቱ ክለቦች ወቅታዊ ሁኔታ በደረጃ ብቻ ሳይሆን በሌሎች መለኪያዎችም ሲታይ እጅግ የተራራቀ ነው። ወልዋሎ እስካሁን ካልተሸነፉት የሊጉ አራት ክለቦች መሀከል አንዱ ሲሆን መከላከያ ሶስት ጊዜ ሽንፈትን ቀምሷል። ግብ በማስቆጠር ረገድም ያለፈው ሳምንት የሊጉ መሪዎች ሶስተኛ ደረጃ ሲኖራቸው መከላከያ ሁለት ግቦችን ብቻ በማስቆጠር ከሊጉ ዝቅተኛ ግብ አስቆጣሪ ክለቦች መሀከል አንዱ ሆኗል። በመሆኑም ዛሬ ዓዲግራት ላይ በኢ/ዳኛ ቴውድሮስ ምትኩ መሪነት በሚደረገው ጨዋታ በተቃራኒ አቅጣጫ እየተጓዙ ያሉ ተጋጣሚዎች የሚገናኙ ይሆናል። 

የጉዳት ዜና ያልተሰማበት ወልዋሌ ዓ.ዩ ግብ ጠባቂውን በረከት አማረን ከሴካፋ መልስ እንዲሁም አማካዩን አፈወርቅ ሀይሉን ከመጠነኛ ጉዳት በኃላ የሚያገኝ ይሆናል። በመከላከያ በኩል አሁንም ማራኪ ወርቁ እና አዲሱ ተስፋዬ ከረጅም ጊዜ ጉዳታቸው ያላገገሙ ሲሆን ከሴካፉ የተመለሰው ግዙፉ ተከላካይ ቴውድሮስ በቀለም ጉዳት ላይ እንደምገኝ ሰምተናል።

በመጀመሪያዎቹ አምስት ሳምንታት ደክሞ በታየው የአማካይ ክፍሉ ላይ ለውጥ ሳያደርግ የቆየው መከላከያ ሳምንት ኦጉታ ኦዶክን የመጀመሪያ አሰላለፍ ዕድል በመስጠት እና ከበሀይሉ ግርማ ጋር በማጣመር አንድ አጥቂ ቀንሶ ከ 4-4-2 ወደ 4-2-3-1 አሰላለፍ መጥቶ ታይቷል። በዚህም መከላከያዎች ከሌላው ጊዜ በተሻለ መሀል ሜዳ ላይ ይወሰድባቸው የነበረውን የቁጥር ብልጫ በማጣጣትም ሆነ ከአጥቂዎች ጀርባ ቡድኑ ይተወው የነበረውን ሰፊ ክፍተት በማጥበብ በኩል ለውጥ ማሳየት ችለዋል። ምን አልባት ዛሬም ቡድኑ በተመሳሳይ መልኩ መቅረብ ከቻለ መሀል ላይ ሁለት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮችን የሚጠቀመውን ወልዋሎን ለመቋቋም ዕድል የሚሰጠው እንደሚሆን ይታመናል። ከዚህ ውጪ አሁንም በጥንካሬው እየዘለቀ የሚገኘው የወልዋሎ የሁለቱ መስመሮች የማጥቃት ሂደት በከድር ሳሊህ እና ፕሪንስ ሰቨሪንሆ አማካይነት እየተመራ ከሚፈጥረው ጫና ባለፈ መከላካዮች የመስመር ተከላካዮቻቸው እንደልብ ወደፊት እንዳይሄዱ ማድረግ የሚችል አቅም ይኖረዋል።  የፊት አጥቂው ሙለአለም ጥላሁንም በቅርብ ጨዋታዎች ላይ ወደ ጥሩ አቋም መመለስ ለቡድኑ የፊት መስመር  ተጨማሪ ጉልበት እየሆነ መምጣት ለመከላከያዎች ሌላ ስጋት የሚፈጥር ይሆናል።

ወላይታ ድቻ ከ መቐለ ከተማ

በመሀላቸው የአንድ ነጥብ ልዩነት ብቻ ያለው መቐለ ከተማ እና ወላይታ ድቻ በፌ/ዳኛ ዳንኤል ግርማይ የመሀል ዳኝነት ከሚመራው የዛሬው ጨዋታ በፊት በሰበሰቧቸው ነጥቦች 11ኛ እና 13ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል። በተለይ ሁሉንም የስድስት ሳምንት ጨዋታዎች ያደረጉት ድቻዎች በመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥብ መሰብሰብ ከቻሉ በኃላ አምስት ነጥቦች ላይ መቆማቸው ቀጣዩን ጉዟቸውን ጥያቄ ውስጥ የሚከተው ሆኗል። አራቱን ሳምንት  ያለሽንፈት በመጓዝ ያሳለፈቱ መቐለዎችም እንደተጋጣሚያቸው ሁሉ ጥሩ በሚባል መልኩ ሊጉን ቢጀምሩም ሜዳቸው ላይ በደደቢት መሸነፋቸው በሰንጠረዡ ቁልቁል እንዲንሸራተቱ አድርጓቸዋል። በመሆኑም ጨዋታው ሁለቱም ቡድኖች ጥሩ ወደነበረው አጀማመራቸው ለመመለስ የሚጥሩበት እንደሚሆን ይጠበቃል። 

የቡድኑ አምበል ተክሉ ታፈሰ ፣ በዛብህ መለዮ እና ዳግም በቀለ ከወላይታ ድቻ በኩል በጉዳት ከጨዋታው ውጪ የሆኑ ተጨዋቾች ሲሆኑ በመቐለ ከተማ በኩል የመሀል ተከላካዩ አሌክስ ተሰማ ጨዋታውን የመጀመር ጉዳይ አጠራጣሪ ከመሆኑ ሌላ የተሰማ የጉዳት ዜና የለም።

የወላይታ ድቻ በርካታ የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ችግር ፀጋዬ ብርሀኑ ከሴካፋ መመለሱን ተከትሎ የተወሰነ መሻሻል ይታይበታል ተብሎ ይጠበቃል። ሆኖም ቡድኑ አሁንም የመስመር አጥቂዎቹን እና ተመላላሾቹን እንቅስቃሴ ሌላው ደካማ ጎኑ ተደርጎ የሚወሰደውን በመሀል አማካዮቹ እና በጃኮ አራፋት መሀከል የሚታይ ሰፊ ክፍተት ለማካካስ በሚያስችል መልኩ መቃኘት ይጠበቅበታል። ይህ የማይሆን ከሆነ ግን እዚህ ቦታ ላይ በሜዳው ጎን አማኑኤል ገ/ሚካኤል ፣ ያሬድ ከበደን እና መድሀኔ ታደሰን የሚጠቀመው መቐለ ከተማ ሰፊ የመጫወቻ ክፍተት ማግኘቱ የማይቀር ነው። በተለይም ያሬድ ከድቻ የመሀል አማካዮች ፊት የእንቅስቃሴ ነፃነትን የሚያገኝ ከሆነ ለአጠቃላይ የመቐለ የማጥቃት ሂደት መቀላጠፍ ወሳኝ ሚና መጫወት ይችላል። ከዚህ ውጪ የወላይታ ድቻ ጠንካራ ጎን በመሆን ስድስቱን ሳምንታት የዘለቀው ጃኮ አራፋት በዚህም ጨዋታ ከሚካኤል ደስታ እና ዐመለ ሙልኪያስ ጀርባ እና ከመሀል ተከላካዬቹ ፊት የሚያደርገው የጎንዮሽም ሆነ ቀጥተኛ እንቅስቃሴ ለራሱም ሆነ ለሁለቱ የድቻ የመስመር አጥቂዎች የማጥቃት አጋጣሚን ለመፍጠር እጅግ ወሳኝ እንደሚሆን ይታሰባል።

አዳማ ከተማ ከ ፋሲል ከተማ

ፌ/ዳኛ ቢኒያም ወርቅአገኘው በዋና ዳኝነት የሚመሩት ይህ ጨዋታ መልካም በሚባል አጀማመር ላይ የሚገኙ ክለቦችን የሚያገናኝ ነው ማለት ይቻላል። ሁለቱ ቡድኖች በእኩል ዘጠኝ ነጥብ ላይ ቢገኙም አንድ ቀሪ ጨዋታ ያለው ፋሲል ከተማ በግብ ክፍያ በልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። ከነጥባቸው ባሻገር አዳማ ከተማ እና ፋሲል ከተማ ሁለት ጨዋታዎችን በማሸነፍ እና ሶስት ጊዜ አቻ በመለያየትም ይመሳሰላሉ። አምና በመጨረሻው ሳምንት ፋሲል ከተማን አስተናግደው 2-1 ማሸነፍ የቻሉት አዳማ ከተማዎች ሳምንት ሜዳቸው ላይ ድሬደዋን አስተናግደው ያለግብ ሲለያዩ ፋሲሎች ወላይታ ድቻን 1-0 መርታታቸው የሚታወስ ነው። 

አዳማ ከተማ አጥቂው ሚካኤል ጆርጅን በጉዳት የሚያጣ ሲሆን የቡልቻ ሹራ እና የደሳለኝ ደባሽ መሰለፍም እርግጥ አይደለም። በፉሲል ከተማ በኩል ደግሞ ያሬድ ባየህ እና ይስሀቅ መኩሪያ መኩሪያ በጉዳት ጨዋታው እንደሚያልፋቸው ሰምተናል።

ይህ ጨዋታ በሳምንቱ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መሀከል ጥሩ ፉክክር እና እንቅስቃሴ የሚታይበት ሊሆን እንደሚችል መናገር ይቻላል። የፋሲል ከተማ በተለይ ከሜዳ ውጪ በሚደረጉ ጨዋታዎች ላይ በፈጣን የማጥቃት ሽግግር ሁለቱን መስመሮቹን በመጠቀም ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ሰብሮ በመግባት ዕድሎችን ለመፍጠር የሚያደርገው ጥረት እና አዳማ ከተማ በጠንካራ የአማካይ ክፍሉ ላይ ተመስርቶ በኳስ ቁጥጥር ዕድሎችን የሚፈጥርበት አኳኃን እርስ በእርስ የሚገናኙበት ጨዋታ መሆኑ ለዚህ ነጥብ ማስረጃ መህምን ይችላል።  በዚህ አቀራረባቸው ሁለቱም ቡድኖች ከሴካፋ መልስ የሚያጎኟቸው ተጨዋቼች ሚና ቀላል የሚባል አይደለም። በጉዳት ሲታመስ በቆየው የአሰልጣኝ ተገኔ ነጋሽ የፊት መስመር ላይ ዳዋ ሁቴሳ መመለሱ እጅግ ወሳኝ ይሆናል። ላለፉት ሁለት ጨዋታዎች በሱራፌል ዳኛቸው ብቻ ላይ ተመስርቶ የነበረው የቡድኑ የፈጠራ ምንጭም የከንአን ማርክነህን መመለስ ተከትሎ ተገማችነቱ የሚቀንስበት እና በቁጥር ከፍ ያሉ የማግባት አጋጣሚዎችን ለመፍጠር ሚታደልበት ዕድል ሰፊ ነው። በፋሲል ከተማ በኩል ጥሩ የሚባሉ የመልሶ ማጥቃት የጨዋታ ሂደቶችን ከፈጠሩ  እና በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ላይ በቁጥር በልጠው ከተገኙ በኃላ የሚባክኑ ኳሶችን በአግባቡ ለመጠቀም የአብዱርሀማን ሙባረክ መኖር የሚሰጠው ጥቅም እጅግ ከፍ ያለ ነው። ተጨዋቹ ራሱ ከምፈጠሩት ዕድሎች ግብ በማስቆጠርም ሆነ ፊሊፕ ዳውዝን በቅብብል በማግኘት በኩል ለቡድኑ ወሳኝ አገልግሎት እንደሚሰጥ ይጠበቃል።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አርባምንጭ ከተማ

አምና በሊጉ የመክፈቻ ጨዋታ አዲስ አበባ ላይ በተገናኙበት  ጊዜ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከጨዋታ ብልጫ ጋር 3-0 ማሸነፍ መቻሉ የሚታወስ ነው።  አርባምንጭ ከተማ ዘንድሮ እስካሁን ወደ አዲስ አበባ ስቴድየም በመጣበት ብቸኛ አጋጣሚ በኢትዮጵያ ቡና 2-0 መሸነፉ ይታወሳል። ሆኖም ከዛ በኃላ ባደረጋቸው ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል። ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ከሁለት ተከታታይ ድሎች በኃላ ያለፈው ማክሰኞ በሸገር ደርቢ ነጥብ መገራቱ የሚታወስ ነው። በመሆኑም ዛሬ በፌ/ዳኛ ሰለሞን ገ/ሚካኤል የመሀል ዳኝነት 10፡00 ላይ በሚጀምረው ጨዋታ ሁለቱ ቡድኖች በስድስተኛው ሳምንት ካስመዘገቡት የአቻ ውጤት በኃላ እርስ በእርስ የሚገናኙበት ይሆናል። 

ሳልሀዲን ሰይድ ፣ ናትናኤል ዘለቀ እና ታደለ መንገሻ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል የረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጨዋችምች ሲሆኑ አሜ መሀመድም በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ተጎድቶ በመውጣቱ ለዚህ ጨዋታ የማይደርስ ይሆናል። አርባምንጭ ከተማዎችም አማኑኤል ጎበናን እና አንድነት አዳነን በተመሳሳይ በጉዳት ሳብያ የማይጠቀሙ ይሆናል። 

የአሜ መሀመድን ጉዳት ተከሎ ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮው የውድድር አመት እየተገበረ ባለው የኳስ ቁጥጥርን መሰረት ባደረገው አጨዋወት ውስጥ የፊት መስመሩ ላይ የተጨዋች ለውጥ አድርጎ የሚታይበት ጨዋታ ይሆናል። እዚህ ቦታ ላይ ቡድኑ አዳነ ግርማን የሚጠቀም ከሆነ እንደወትሮው ሁሉ ከቀጥተኛ እና ተሻጋሪ ኳሶች የግብ ዕድሎችን ወደመጠቀሙ ሊያደላ ይችላል። በሌላ ጎን ደግሞ አዳነ በአማካይ መስመር ላይ ካለው የጨዋታ ልምድ አኳያ ከፊትም ሄኖ ከአብዱልከሪም ኒኪማ እና ምንተስንምት አዳነ ጋር የሚኖረውን የቅብብል ሂደት ሊያፋጥን እንደሚችል መናገር ይቻላል። ከዚህ ውጪ ግን ቅዱስ ጊዬርግስ በቦታው ላይ የሀሰተኛ ዘጠኝ ቁጥር ሚናን ሊወጣ የሚችል ተጨዋች ለመጠቀም ከሞከረ ምንአልባትም ለቡድኑ ሌላ አማራጭ የሚሰጥ አቀራረብን ለመመልከት ዕድል የሚያስገኝ ይሆናል። ከሴካፋ መልስ የእንዳለ ከበደን አገልግሎት የሚያገኙት አርባምንጮች ደግሞ የተጨዋቹ መመለስ ከአማካይ ክፍላቸው የሚነሳውን የመስመር ጥቃት የተሻለ ጥንካሬን ሊያላብሰው እንደሚችል መናገር ይቻላል። ከዚህ ውጪ የምንተስኖት አበራ እና አለልኝ አዘነ ጥምረት የተጋጣሚያቸውን የኳስ ቁጥጥር ለማፈንም ሆነ በፈጠራው ረገድ ከሙሉአለም መስፍን ጋር የሚፋለመውን ወንድሜነህ ዘሪሁንን በማገዙ በኩል የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለቡድኑ ሚዛን መጠበቅ እጅግ ወሳኝ እንደሚሆን ይጠበቃል። ነገር ግን እንደ ሸገር ደርቢ ሁሉ መሀል ሜዳው ላይ ሁለቱም ቡድኖች የሚጠቀሟቸው ተጨዋችምች መበራከትን ተከትሎ በርካታ የተቆራረጡ ቅብብሎችን እንዳንመለከት የሚያሰጋ ቢሆንም የቡድኖቹ የመስመር አጥቂዎች እና የመስመር አማካዮች የማጥቃት እንቅስቃሴ ጨዋታውን በሁለቱ ክንፎች በኩል ፍጥነት የተላበሰ እንዲሆን ለማድረግ እንደሚረዳ ይታሰባል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *