የወልዲያ ተጫዋቾች ነገ ወደ ክለቡ ይመለሳሉ

የወልዲያ ስፖርት ክለብ አመራር እና የቡድኑ አባላት ዛሬ ረፋድ ላይ ባደረጉት ውውይት ከስምምነት ላይ በመድረሳቸው የቡድኑ አባላት ወደ ወልዲያ በማቅናት መደበኛ ልምምዳቸውን በነገው ዕለት እንደሚጀምሩ ታውቋል።

ወልዲያ በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 12ኛ ሳምንት ጅማ ላይ በጅማ አባጅፋር 1-0 በሆነ ውጤት ከተሸነፈበት ማግስት ጀምሮ በወልዲያ በተፈጠረው ወቅታዊ አለመረጋጋት የተነሳ ያለፉትን አስራ አምስት ቀናት እንደ ቡድን ልምምዶችን ሳያደርግ የቀረ ሲሆን ቡድኑ በጊዜያዊነት በመበተኑም በሊጉ መጫወት የነበረበትን ሦስት ጨዋታዎችን ሳያከናውን መቅረቱ ይታወቃል።

የክለቡ አመራሮች ለመገናኛ ብዙሀን ከክለቡ እውቅና እና ፍቃድ ውጭ የቡድኑ አባላት ከሆቴል ጠፍተው ሄደዋል ሲሉ ተጫዋቾቹ ደግሞ ምንም አይነት ከለላ እና ዋስትና በሌለበት እንዴት እዛ ልንቆይ እንችላለን በሚል በሁለቱ አካላት መካከል አለመግባባት መፈጠሩን ተከትሎ ትላንት አዲስ አበባ ላይ የክለቡ አመራሮች እና የቡድኑ አባላት በቀጣይ የክለቡ ጉዞ ዙርያ ይወያያሉ ተብሎ ሲጠበቅ በተለያዩ ምክንያቶች ሳይካሄድ ቢቀርም ዛሬ ከረፋድ ጀምሮ ሰፊ ውይይት ካደረጉ በኋላ ከስምምነት ላይ በመድረሳቸው የወልዲያ እግርኳስ ቡድን ከነገ ጀምሮ ወደ ወልዲያ በማቅናት ልምምድ እንደሚጀምሩ ሰምተናል።

ቡድኑ ዝግጅቱን አጠናክሮ በመቀጠል በቀጣይ 15ኛ ሳምንት ወደ ወላይታ ሶዶ በማቅናት ከወላይታ ድቻ ጋር በሚያደርገው ጨዋታ ወደ ውድድር ይመለሳል ተብሎ ይጠበቃል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *