ስሞሃ በኡመድ ግብ ወደ አሸናፊነት ተመልሷል

በ24ኛው ሳምንት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ሁለቱ ኢትዮጵያዊያኖች የሚጫወቱባቸው ክለቦች ድል ቀንቷቸዋል፡፡ ስሞሃ እና ፔትሮጀት ከሜዳቸው ውጪ በተመሳሳይ 1-0 ማሸነፍ ችለዋል፡፡ ውጤቶቹ እምብዛም የደረጃ ለውጥ ባያስከትሉም በ23ኛ ሳምንት ሁለቱም ክለቦች ተሸንፈዋል፡፡

ካይሮ ላይ አርብ በተደረገ ጨዋታ ስሞሃ ከሜዳው ውጪ ታላል ኤል ጋይሽን 1-0 ረቷል፡፡ ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት ጨዋታ የእንግዶቹን የድል ግብ ኡመድ ኡኩሪ በ42ኛው ደቂቃ አስገኝቷል፡፡ ታርቅ ጠሃ አብዱልሃሚድ ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ የጋይሽ ተከላካዮች ማውጣት አለመቻላቸውን ተጠቅሞ ኡመድ በግንባሩ በመግጨት ኳስ እና መረብን አገናኝቷል፡፡ ይህቺ ግብ ለኡመድ 4ተኛ የሊግ ግብ ስትሆን ሰማያዊ ሞገዶቹ ከሁለት ጨዋታ ሽንፈት በኃላ ወደ አሸናፊነት መመለስ ችለዋል፡፡ ያለፉትን ሳምንታት በፔትሮጀት 2-0 እና በዛማሌክ 1-0 የተሸነፉት ስሞሃዎች ጋይሽ ላይ የተቀዳጁት ድል ወሳኝ ነው፡፡ ኡመድ በ78ኛው ደቂቃ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክቷል፡፡ ስሞሃ በሳምንቱ መጀመሪያ ዋና አሰልጣኙ ታላት የሱፍ በገዛ ፍቃዳቸው ከስራቸው መልቀቃቸውን ተከትሎ ሚሚ አብዱልራዛክ ተክተዋል፡፡ በውድድር አመቱ ለስሞሃ ሶስተኛ አሰልጣኝ የሆኑት ሚሚ በመጀመሪያ ጨዋታቸውን ማሸነፍ ችለዋል፡፡

በዋዲ ደግላ በ23ተኛው ሳምንት የተሸነፈው ፔትሮጀት በ24ኛው ሳምንት ሙሉ ሶስት ነጥብን ማሳካት ችሏል፡፡ ሐሙስ ላይ ካይሮ ላይ በተደረገ ጨዋታ ፔትሮጀት አል ናስርን 1-0 አሸንፏል፡፡ ኢትዮጵያዊው ፈጣሪ አማካይ ሽመልስ በቀለ ከአምስት ጨዋታ በኃላ ፔትሮጀትን በአምበልነት ሳይመራ ቀርቷል፡፡ በጨዋታው ሽመልስ በመጀመሪያው አጋማሽ መጠናቀቂ ላይ የቢጫ ካርድ የተመለከተ ሲሆን የስዌዙን ክለብ የድል ግብ መሃመድ ሳልም በ68ኛው ደቂቃ አስቆጥሯል፡፡ ሽመልስ በ75ኛው ደቂቃ በካሪም ታርቅ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ የአል ናስሩ ኮትዲቯራዊ አማካይ ፍራንክ ኤልቪስ በሁለት ቢጫ በ88ኛው ደቂቃ ከሜዳ በመሰናበቱ አል ናስር ቀሪዎቹን ደቂቃዎች በ10 ተጫዋቾች ለመጨረስ ተገዷል፡፡

ስሞሃ በደረጃ ሰንጠረዡ በ38 ነጥብ 5ተኛ ሲሆን ፔትሮጀት በ31 ነጥብ 10ኛ ነው፡፡ ሊጉን አል አሃሊ በ63 ነጥብ ሲመራ ኤስማኤሊ በ46፣ አል መስሪ እና ዛማሌክ በእኩል 42 ነጥቦች ከ2-4 ያሉትን ደረጃዎች ይዘዋል፡፡ የፊታችን ሰኞ በ25ኛ ሳምንት የሊግ ጨዋታ ፔትሮጀት ዛማሌክን ሲያስተናግድ የስሞሃ ጨዋታ ተጋጣሚው ምስር ኤል ማቃሳ ጨዋታ በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ ቅደመ ማጣሪያ የሴኔጋሉን ጄኔሬሽን ፉትን ስለሚያስተናግድ ለሌላ ግዜ ተሸጋግሯል፡፡

የኡመድን ግብ ለመመልከት ይህንን ይከተሉ – https://­www.youtube.com/­watch?v=muYE6I7LlEU

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *