ደደቢት በዝውውር መስኮቱ ተጫዋች አያስፈርምም

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ የውድድር ዘመን አጋማሽን በ29 ነጥቦች በቀዳሚነት ያጠናቀቀው ደደቢት በአሁኑ ወቅት ክፍት በሆነው የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ምንም ተጫዋች እንደማያስፈርም ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል።

ክለቡ በሁለተኛው የውድድር ዘመን አጋማሽ ራሱን ለማጠናከር ተጨማሪ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ በማምጣት ለዋንጫ የሚያደርገውን ጉዞ ያጠናክራል ተብሎ ቢጠበቅም በተቃራኒው ምንም አይነት አዲስ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ የማምጣትም ሆነ ያሉትንም የመቀነስ ፍላጎት እንደሌለው የክለቡ ስራ አስኪያጅ አቶ ሚካኤል አምደመስቀል ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል። በአስተያየታቸውም “የውድድር ዘመኑን አሁን ባለን የተጫዋቾች ስብስብ በጥሩ ሁኔታ ማጋመስ ችለናል። ይህን ጥንካሬ ይዘን ሁለተኛውን አጋማሽ እንቀጥላለን እንጂ አዲስ ተጨዋች በማምጣት የተቀናጀውን ቡድን እንደ አዲስ አንሰራም።” ብለዋል።

ከደደቢት ጋር በተያያዘ ሌላ ዜና ክለቡ ከጅማ አባ ጅፋር ጋር ባደረገው ጨዋታ ላይ ቀይ ካርድ የተመለከተው ጌታነህ ከበደ ጌታነህ ከበደ የ4 ጨዋታ ቅጣት እንደተላለፈበት የሚታወስ ነው። ሆኖም ክለቡ ባቀረበው የይቅርታ ጥያቄ መሰረት እስካሁን ከአራት ጨዋታ ሦስቱ ያለፈው ጌታነህ ፌዴሬሽኑ ጥያቄውን በመቀበል በ16ኛው ሳምንት ሶዶ ላይ ወላይታ ድቻን በሚገጥመው የደደቢት ስብስብ ውስጥ እንዲካተት ፈቃድ ሊሰጠው እንደሚችል ተሰምቷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *