ፌዴሬሽኑ የዳኞች እና ታዛቢዎች ማህበር ውሳኔን በማስቀየር ዙርያ ሲመክር አመሸ

ምሽቱን የተካሄደው የፌዴሬሽኑ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አስቸኳይ ስብሰባ በወቅታዊው የዳኞች እና ታዛቢዎች ውሳኔ ዙርያ ውይይት ሲያደርግ ቆይቶ ለውሳኔ በይደር ለነገ ተላልፏል። 

ከኢትዮዽያ ዳኞች እና ታዛቢዎች የሙያ ማህበር ከፍተኛ ተቃውሞ ሲያስተናግድ የዋለው ፌዴሬሽኑ ከ11:00 ጀምሮ ባደረገው አስቸኳይ የስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ላይ ቅዳሜ የሚደረገው የአስመራጭ ኮሚቴ ምርጫን አስመልክቶ ከተወያየ በኋላ የዳኞች እና ታዛቢዎች የሙያ ማህበር እንደቅድመ ሁኔታ መተግበር ይገባቸዋል ያላዋቸው ነጥቦች ላይ ተግባራዊ የሆነ እርምጃ እስካልተወሰደ ድረስ ከነገ ጀምሮ ለቀጣዮቹ 3 ሳምንታት ማንኛውም ውድድር ላለመዳኘት ከውሳኔ የመድረስ አቋም ላይ ትኩረት አድርገዋል።

በስብሰባው ላይ ከነበሩ ተሰብሳቢዎች መካከል በተለይ ፕሬዝደንቱ አቶ ጁነይዲ ባሻ እና አቶ አበበ ገላጋይ ውሳኔው ተገቢ አይደለም ፤ ውድድሮች መቋረጥ የለባቸውም በማለት ውሳኔውን ለማስቀልበስ የሚያስችሉ የተለያዩ ሀሳቦች ሲያነሱ የነበረ ቢሆንም በአንዳንድ የስራ አስፈፃሚ አባላት ደግሞ ውሳኔው ተገቢ መሆኑን አንስተው ሲከራከሩ አምሽተው ከውሳኔ ሳይደርሱ ስብሰባው ተጠናቋል።  የመጨረሻ የፌዴሬሽኑን አቋም የሚገልፅ ውሳኔ ለመስጠትም ነገ ማለዳ 12:30 ጀመሮ ለመነጋገር ቀጠሮ ይዘው የተለያዩ ሲሆን ከነገ ስብሰባቸው መጠናቀቅ በኋላ የፌዴሬሽኑን አቋም የሚያንፀባርቅ ጋዜጣዊ መግለጫ ሊሰጥ እንደሚችል ሰምተናል።

በሌላ በኩል ነገ ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ በጁፒተር ሆቴል የ16 የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች አመራሮች በተገኙበት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ ሊደረግ በታሰበው የውይይት መድረክ ላይ ነገ የሚለወጥ ሀሳብ ካልኖረ በስተቀር ጋዜጠኞች እንዳይገኙነመ በዝግ እንዲካሄድ ውሳኔ ላይ መድረሳቸውን ሰምተናል።