“ፊፋ እና ካፍ በመከላከያ እና ወልዋሎ ጨዋታ ዙርያ ውሳኔ እንድናሳውቅ ደብዳቤ ልከዋል” ልዑልሰገድ በጋሻው

በኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ 22ኛ ሳምንት ሚያዚያ 22 ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በመከላከያ እና በወልዋሎ ጨዋታ ላይ በ83ኛው ደቂቃ የዕለቱ ዳኛ ፌደራል ዳኛ ኢያሱ ፈንቴን የወልዋሎ ተጫዋቾች እና የቡድን መሪው አቶ ማሩ ገብረፃድቅ በዳኛው ላይ ባደረሱት ድብደባ ጨዋታው መቋረጡ ይታወቃል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላም ጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት አግኝቶ በዓለም አቀፍ ሚድያዎችም ጭምር ሲዘገብ ቆይቷል።

ክስተቱ ከተፈጠረ ከአንድ ሳምንት በላይ ቢያስቆጥርም እስካሁን ውሳኔ ያልተሰጠበት ሲሆን ዛሬ በፌዴሬሽኑ እና በዳኞች እና ታዛቢዎች ማኅበር መካከል በተደረገው ስብሰባ ላይ የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ልዑልሰገድ በጋሻው የእግርኳሱ የበላይ አካል ፊፋ እና የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) በዳኛው ላይ ድብደባ የፈፀሙት አካላት ላይ የሚወሰደውን የዲሲፒሊን ውሳኔ የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እንዲያሳውቀው ደብዳቤ መላኩን ተናግረዋል። የፌዴሬሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ ግን ስለ ደብዳቤው መላክ የሚያውቁት ጉዳይ እንደሌለ ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና ዛሬ ምሽቱን ስብሰባ የሚቀመጠው የዲሲፕሊን ኮሚቴ አባላት የጨዋታው ኮሚሽነር ይድነቃቸው ዘውገ ያቀረቡትን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል ።