“በቀጣይ ጨዋታዎች ከወራጅነት ስጋት ለመራቅ በትኩረት እንጫወታለን ” ዘነበ ፍስሃ

አሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ ወላይታ ድቻን በዋና አሰልጣኝነት ከተረከቡ ወዲህ በአፍሪካ ኮፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመርያው ተሳትፎ ታሪክ በመስራት የምድብ ድልድል ለመግባት የመጨረሻው ወሳኝ ምዕራፍ ደርሶ ከውድድሩ ውጭ የሆነው ወላይታ ድቻ በሊጉም ከፍተኛ መሻሻል በማሳየት ከወራጅ ቀጠናው መውጣት ችሎ ነበር ። ሆኖም በሁለተኛው ዙር ባደረጋቸውን አብዛኛው ጨዋታዎች ነጥቦችን እየጣለ ራሱን ዳግም በወራጅ ቀጠና ፉክክር ውስጥ እንዲያገኘው ሆኗል። የቡድኑን ወቅታዊ አቋም አስመልክቶ እና ከሜዳ ውጭ በሚሰሙ አንዳንድ ችግሮች ዙርያ ከአሰልጣኝ ዘነበ ፍስሃ ጋር ያደረግነውን አጭር ቆይታ እንደሚከተለው አሰናድተነዋል

ወላይታ ድቻ ከሁለተኛው ዙር አንስቶ ነጥቦችን ደጋግሞ በመጣል አሁን አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። የዚህ ውጤት ማጣት መንስኤው ምንድነው ? 

እስካሁን ድረስ ነጥብ መጣል በማይገባን ጨዋታዎች ነው ነጥብ ስንጥል የቆየነው። በጣም ጥሩ ሆነን እየተጫወትን ፣ የጎል አጋጣሚዎችን እየፈጠርን ነገር ግን ግብ የማስቆጠር ችግር ስላለብን ነው ነጥብ የጣልነው። እንደግምገማችን ዋናው እና ትልቁ ነጥብ በሁለተኛው ዙር ተጨዋቾቻችን የተባሉትን ነገር ያለማድረግ ችግር እየተንፀባረቀባቸው መሆኑ ነው። ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ አለመሆን ፣ አድርጉ የተባሉትን ነገር ትተው ሌላ ነገር እያደረጉ በመሆኑ ውጤት ልናጣ ችለናል። ዞሮ ዞሮ አሁን አጣብቂኝ ውስጥ በገዛ እጃችን ገብተናል። አሁን ከተጫዋቾቻችን ጋር ተነጋግረን ችግሩን ለመፍታት እየሰራን ነው። በተለይ በተለይ ከኮፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎ በኋላ ቡድኑ ላይ እየተንፀባረቀ ያለው ነገር ጥሩ አይደለም። ተጨዋቾችም ራሳቸውን ማየት ያልቻሉበትን ሁኔታ በየጨዋታው እያየን ነው ያለነው።

ከኮፌዴሬሽን ዋንጫ ጨዋታዎች በኋላ በተጨዋቾቹ ላይ ከልክ ያለፈ በራስ መተማመን ይታያል። ይህ መሆኑ በቡድኑ ማጤት ላይ ተፅዕኖ አላደረገም ?

አዎ ለማስተካከል በየዕለቱ ነው የምንነጋገረው። ዛሬ ተጫወትን  ነገ ከዛ ጨዋታ ተነስተን ገምግመን ስራዎችን እየሰራን ነው። ለማስተካከል በየዕለቱ ነው የምንነጋገረው። ሆኖም ከጨዋታ በፊት ከተነጋገርን በኃላ ሜዳ ውስጥ ገብተን የምንመለከተው ነገር አንድ ሊሆን አልቻለም። ከተባሉት ውጪ ነው እየሰሩ የሚገኙት። ያ ነው ውጤት እያሳጣን እየመጣ ያለው ። ከትላንት ወዲያ ቁጭ ብለን ብዙ ነገሮችን አውርተናል። አሁን ወደ ስራ ገብተናል። እንግዲህ ከአሁን በኋላ ያለውን ነገር በተገቢ ሁኔታ ታክቲካሊ ዲሲፕሊንድ ሆነው እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ከማስጠንቀቂያ ጭምር ነግረናቸዋል። እነሱም አምነው የተቀበሉት ጉዳይ ነው ።

በአሰልጣኙ እና በተጨዋቾቹ መሀል አለመግባባት አለ የሚል ወሬ ይናፈሳል። ምን ያህል እውነት ነው ?

እኔ ከማንም ተጨዋች ጋር ያለመግባባት ችግር የለብኝም። ምክንያቱም ከእኔ ጋር አለመግባባት የሚፈጥርበት ምክንያት ስለሌለ ። እኔ የመጣሁት ቡድኑ 16ኛ ደረጃ ላይ ሆኖ አንደኛው ዙር አጋማሽ ላይ ነበር። ስለዚህ ማንም ከእኔ ጋር ያለመግባባት የሚፈጠርበት ምክንያትም ርዕስም የለም። በጉዳት የሚቀመጡ ልጆች በጉዳት ይቀመጣሉ ፣ ልምምድ ላይ በሚያሳዩት አቋም ጥሩ የሆኑትን ጨዋታ ላይ አሰልፋለው። ከዚህ ውጪ ሁሉም በልምምድ ላይ በሚያሳየኝ ብቃት ነው የምጠቀመው። እስካሁን ድረስ እኔ ከመጣው በኋላ ሜዳ ገብተው የማያውቁ ልጆች ጭምር ነው እያጫወትን ያለነው። ስለዚህ  ማንም ሰው ከእኔ ጋር ላይግባባ የሚችልበት ምክንያት የለም የሚያገናኘን ስራ ብቻ ነው ።

በውሳኔ አሰጣጥ ለምሳሌ በተጨዋች ቅያሪ እና በመጀመሪያ አሰላለፍ  ላይ ጣልቃ ገብነት አለ በክለቡ አመራሮች እና ደጋፊዎች በኩል ?

በፍፁም ! እንደነዚህ ያሉ ነገሮች እስከዛሬም አልተደረጉም ወደ ፊትም አይደረጉም። ምክንያቱም ልምምድ አይቼ ባሳዩት አቋም ነው እስካሁን እየተጠቀምኩ ያለሁት። ከአሰልጣኝ አባላቶቼ ጋር ያለውን ነገር በመነጋገር ነው ለውጥም ሲኖር ተጨዋች የምንቀይረው ። የመጀመሪያ አሰላለፍ የማውጣት ድርሻው የእኔ ነው። ይህንንም በአግባቡ እየሰራው ነው ። ማንም ሰው በእኔ ስራ ላይ ጣልቃ የገባ እና እጁን የከተተ ሰው የለም ።

ወላይታ ድቻ በቀጣይ ቀሪ ጨዋታዎች ራሱን ከወራጅ ቀጠና ስጋት እንዲወጣ ምን እየተሰራ ነው ?

የተለየ የሰራነው ነገር የለም። ሆኖም ከአሁን በኋላ ያለው ውጤት እያንዳንዱ ነገር በቅርበት እየተከታተልን ተጨዋቾቹ ሜዳ ላይ የሚባሉትን ነገር ብቻ እንዲያደርጉ አስጠንቅቂያለው። እንግዲህ ቀጣይ በጨዋታዎች ሁሉ ትኩረት አድርገን ጥሩ ውጤት አስመዝግበን ካለንበት የመውረድ ስጋት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ ለመውጣት ነው እየተነጋገርን ያለነው።