የ17 ዓመት በታች የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ በነሀሴ ወር ይካሄዳል

በታንዛንያ አስተናጋጅነት በ2019 ለሚከናወነው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ የማጣርያ ጨዋታዎች በክፍለ አህጉር ተከፋፍለው ይከናወናሉ። በሴካፋ ዞን የሚደረገው የማጣርያ ውድድርም በታንዛንያ አስተናጋጅነት ከነሀሴ 4 – 20 ይካሄዳል። 

የአፍሪካው ውድድር አስተናጋጅ በሆነችው ታንዛንያ አስተናጋጅነት በሁለት ምድብ ተከፍሎ በሚከናከነው የዚህ ውድድር ምድብ ድልድል ይህን ይመስላል፡-

ምድብ ሀ፡ ታንዛንያ፣ ሩዋንዳ፣ ቡሩንዲ፣ ሶማሊያ እና ሱዳን

ምድብ ለ፡ ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ጅቡቲ

8 ሀገራት በሚሳተፉበት የ2019 የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ላይ ሴካፋን ጨምሮ ከ7 የክፍለ አህጉር ውድድሮች ቻምፒዮን የሚሆኑ ቡድኖች ሲሸጋገሩ በአፍሪካ ዋንጫው ግማሽ ፍፃሜውን የሚቀላቀሉ ብሔራዊ ቡድኖችም በፔሩ አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የዓለም ዋንጫ የሚያልፉ ይሆናል።

በተመስገን ዳና የሚሰለጥነው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከወራት በፊት በቡሩንዲ በተዘጋጀው የሴካፋ ውድድር ላይ ከምድቡ ሳያልፍ መመለሱ የሚታወስ ነው። በአሰራር ክፍተት ምክንያት ሶስት ተጫዋቾች በእድሜ ተገቢነት ጉዳይ ከውድድሩ እንዲሰናበቱና አንድ ጨዋታ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆን መደረጉም የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።


የኢትዮጵያ ጨዋታዎች

እሁድ ነሃሴ 6

ዩጋንዳ ከ ኢትዮጵያ (ቻማዚ)

ማክሰኞ ነሃሴ 8

ጅቡቲ ከ ኢትዮጵያ (ቻማዚ)

እሁድ ነሃሴ 13

ኢትዮጵያ ከ ደቡብ ሱዳን (ቻማዚ)

ረቡዕ ነሃሴ 16

ኢትዮጵያ ከ ኬንያ (ቻማዚ)