የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን የማጣርያ ዝግጅቱን በቀጣይ ሳምንት ይጀምራል

በታዛንያ አስተናጋጅነት በ2019 ለሚከናወነው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ በሴካፋ ዞን በሁለት ምድብ ተከፍሎ የሚካሄደው የማጣርያ ጨዋታ ከነሐሴ 4-20 በዋናው ውድድር አዘጋጇ ታንዛንያ ይካሄዳል። የኢትዮጵያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን በሀዋሳ ከተማ በቅርቡ ይጀምራል ።

በአሰልጣኝ በተመስገን ዳና የሚመራው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ለአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ላለባቸው ወሳኝ ውድድር በባቱ ከተማ እየተካሄደ ከሚገኘው ከ17 አመት በታች የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የማጠቃለያ ውድድር ላይ ጥሩ አቋም ያሳዩ የተወሰኑ አዳዲስ ተጨዋቾችን በመምረጥ እና አስቀድሞ በሴካፋ ከተመረጡት 17 ተጫዋቾች ጋር በማጣመር ከሰኞ ሐምሌ 16 ጀምሮ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የምልመላ ስራ ካከናወኑ በኋላ ከሐምሌ 18 ጀምሮ 20 ተጨዋቾችን በመያዝ ሙሉ ዝግጅታቸውን በሀዋሳ ከተማ እንደሚያደርጉ ሰምተናል።

በሴካፋ ዋንጫ ላይ የተመስገን ዳና ረዳት በመሆን ያገለገሉት አሰልጣኝ ሙሉጌታ ደሳለኝን በመቀየር የቅዱስ ጊዮርጊስ ከ17 አመት በታች ቡድን ዋና አሰልጣኝ ደረጄ ተስፋዬን በምትኩ መርጠዋል ።
ለኢትዮዽያ ከ17 አመት በታች ብሔራዊ ቡድን ከሚመረጡት 20 ተጨዋቾች መካከል ትውልደ ኢትዮዽያዊው ናኦል ተስፋዬ ከ20 ተጨዋቾች ዝርዝር ውስጥ እንደተካተተ ያረጋገጡልን አሰልጣኝ ተመስገን ዳና ዝግጅታቸውን በበቂ ሁኔታ ለመስራት እንደተዘጋጁ እና በሀዋሳ በሚኖራቸው የዝግጅት ቆይታ የተለያዩ የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎችን እንደሚያደርጉ ገልፀዋል። በሴካፋ ዋንጫ ላይ ያጋጠመው የፓስፖርት ችግር እንዳያጋጥም ከወዲሁ የጥንቃቄ ስራ እንደሚሰሩም ገልፀውልናል ።

የኢትዮዽያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን በምድብ ለ ከዩጋንዳ፣ ኬንያ ፣ ደቡብ ሱዳን እና ከጅቡቲ ጋር የተደለደለ ሲሆን የመጀመርያ ጨዋታውንም እሁድ ነሐሴ 6 ከዩጋንዳ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያካሒድ ይሆናል ።