ኢትዮጵያን ዳኞች ከፍተኛ ግምት ያገኘው የቻምፒየንስ ሊግ ሩብ ፍፃሜ ጨዋታን ይመራሉ

የ2018 የካፍ ቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ የመጀመርያ ጨዋታዎች በዚህ ሳምንት መጨረሻ ይከናወናሉ። ከፍተኛ ግምት የተሰጠው ጨዋታም በኢንተርናሽናል ዳኛ በዓምላክ ተሰማ እና ኢትዮጵያውያን ረዳቶቹ ይመራል። 

በቱኒዚያዎቹ ኃያላን ክለቦች ኤስፔራንስ ደ ቱኒዝ እና ኤቷል ደ ሳህል መካከል ቅዳሜ ምሽት በቱኒዝ ኦሎምፒክ ስታድየም የሚደረገውን ጨዋታ በዓምላክ ተሰማ በዋና ዳኝነት ሲመራው ክንዴ ሙሴ እና ተመስገን ሳሙኤል በረዳትነት አብረውት የሚሰሩ ይሆናል። ሶስቱ ዳኞች በቻምፒየንስ ሊጉ ኢኤስ ሴቲፍ ከ ኤምሲ አልጀር ያደረጉትን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ የመሩ ሲሆን በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ስዋዚላንድ ከቱኒዚያ ያደረጉትን ጨዋታም በዓምላክ እና ተመስገን መምራታቸው የሚታወስ ነው። 

የ2017 ቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ የመጀመርያ ጨዋታን መምራት የቻለው በዓምላክ በዓለም ዋንጫው ከመካፈሉ በተጨማሪ ደረጃቸው ከፍ ያሉ አህጉራዊ ጨዋታዎችን በመዳኘት ላይ ይገኛል።