ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ደረጃውን አሻሻለ

ካፍ ወደ ኤሊት ደረጃ የሚያድጉ ዳኞችን ለመለየት የሚያከናውነው ፈተና ላይ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ ኤሊት ቢ ፈተናን አጠናቆ ወደ ሀገር ቤት ተመልሷል።

በሩዋንዳ በተከናወነው ስልጠና እና ፈተና ላይ ከ36 የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የተወጣጡ ዳኞች ሲሳተፉ ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩም የኢሌት ቢ ስልጠናን አጠናቆ ተመልሷል። ስልጠናው የተለያዩ እርከኖች የነበሩት ሲሆን ከአንዱ እርከን ወደ ሌላኛው ለማለፍ ፈተናዎች ተሰጥተዋል። በአካል ብቃት  ፈተና የተጀመረው ይህ ስልጠና 40 ሜትርን በ6 ሰከንዶች ለስድስት ጊዜ በመደጋገም ማጠናቀቅ የመጀመርያው ሲሆን 75 ሜትርን በ17 ሰከንዶች ማጠናቀቅ እና በ25 ሰከንድ እረፍት 10 ጊዜ ደጋግሞ ማጠናቀቅ መቻል ቀጣዩ ፈተና ነበር።

ይህን ፈተና ያለፉት ሰልጣኞች ወደ ክፍል በመግባት ስልጠና የወሰዱ ሲሆን ስልጠናው በየቀኑ የቪድዮ ፈተናም እንደነበረው ለማወቅ ተችሏል። ከጨዋታ ውጪ ፣ ቴክኒካል ፋውል ፣ በሆልዲንግ፣ በፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የሚፈጠሩ ጥፋቶች እና ኳስን በእጅ የመንካት ጥፋቶች ላይ ያተኮረ ነበር። በዚህም በ2018 የኢንተርናሽናል ባጅ ያገኘው ቴዎድሮስ ምትኩ አህጉራዊ ውድድሮች ላይ ለመዳኘት ዕድል የሚፈጥርለት የኤሊት ቢ ደረጃ ማደግ ችሏል።