የኢትዮጵያ እና ኬንያ ጨዋታ በፓፓ ባካሪ ጋሳማ ዳኝነት ይመራል

የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ሶስተኛ የምድብ ጨዋታዎች በወሩ መጨረሻ ሲከናወኑ ኢትዮጵያ በባህር ዳር ዓለም አቀፍ ስታድየም ኬንያን የምታስተናግድበትን ጨዋታ ጋምቢያዊው የወቅቱ የአፍሪካ ምርጥ ዳኛ ፓፓ ባካሪ ጋሳማ ይመሩታል። 

ባካሪ ጋሳማ ከዚህ ቀደም ሁለት ጊዜ ኢትዮጵያ ያደረገቻቸው ጨዋታዎችን በዳኝነት መርተዋል። ዋልያዎቹ ከ31 ዓመታት በኋላ ባለፉበት የ2013 የአፍሪካ ዋንጫ የመጀመርያ ዙር ተጋጣሚዋ ቤኒንን በድምር ውጤት አሸንፈው ወደ ቀጣዩ ዙር ሲያልፉ ኮቶኑ ላይ የተደረገውን የመልስ ጨዋታ በዳኝነት የመሩ ሲሆን ጨዋታው 1-1 መጠናቀቁ ይታወሳል። ከዓመት በኋላ በ2014 የዓለም ዋንጫ የመለያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ካላባር ላይ በናይጄርያ 2-0 ስትሸነፍ እኚሁ ዳኛ ጨዋታውን መርተዋል። በወቅቱ ቪክቶር ሞሰስ ያስቆጠረው የፍፁም ቅጣት ምትን የሰጡበት ውሳኔን አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው ከጨዋታው በኋላ በሰጡት አስተያየት ተቃውመውት ነበር ” ጨዋታውን ያሸነፈችው ናይጄርያ ሳትሆን ዳኛው ነው። ለኛ ሁለት ፍፁም ቅጣት ምቶች በመከልከል ለናይጄርያ አሳማኝ ያልሆነ ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተዋል” ሲሉ አስተያየት መስጠታቸው ይታወሳል። በሁለቱ ጨዋታዎች በአጠቃላይ 5 ተጫዋቾች በጋሳማ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክተዋል።

ከሁለት ዓመት ወዲህ የተሰረዘው የካፍ የዓመቱ ምርጥ ዳኛ ሽልማትን ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ያሸነፉት ጋምቢያዊው 39 ዓመት ዳኛ መስከረም 30 በባህር ዳር የሚደረገውን ጨዋታ የሀገሩ ዜጎች በሆኑት ሱሌይማን ሶሴህ እና አብዱላዚዝ ጃዎም ረዳትነት የሚመሩ ይሆናል።