ኢትዮጵያ ቡና ላይቤሪያዊ አጥቂ አስመጥቷል

ኢትዮጵያ ቡና የፊት መስመር አማራጩን ያሰፋበትን ዝውውር አጠናቋል።

ካለፈው የውድድር ዓመት አጋማሽ ጀምሮ ኢትዮጵያ ቡናን ማሰልጣን የጀመሩት ፈረንሳያዊው አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ዘንድሮ ቡድናቸውን በራሳቸው መንገድ በመገንባት ላይ ይገኛሉ። አሰልጣኙ እስካሁን ከሀገር ውስጥ እና ከውጪ ስምንት ተጫዋቾችን ያስፈረሙ ሲሆን ከሳምንት በፊት በተለይም ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር ባደረጉት ቆይታ አንድ የመስመር አጥቂ ከላይቤሪያ ለማስመጣት ሀሳቡ እንዳላቸው መናገራቸው ይታወሳል። በዚህም መሰረት በመስመር እና በመሀል አጥቂነት ተሰልፎ የመጫወት ብቃት ያለውን ኩያህ ዴኮ ሾሌን በሁለት ዓመት ውል ማስፈረማቸው ታውቋል።

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመሪያው ላይቤሪያዊ ተጫዋች መሆን የቻለው የ20 ዓመቱ ሾሌ ለሀገሩ ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተሰልፎ የመጫወት ዕድል ነበረው። በክለብ ህይወቱ ደግሞ ለቱኒዚያው ቤዘርቲን ከ23 ዓመት በታች ቡድን የተጫወተ ሲሆን ወደ ፈረንሳዩ የሁለተኛ ዲቪዚዮን ክለብ ቱር ለማምራት ሞክሮ ዝውውሩ ባለመሳካቱ ለሌላው የቱኒዚያ ክለብ ስታድ ጋቢሴን ተጫውቶ አሳልፏል። ኢትዮጵያ ቡና የፊት መስመሩን ለማጠናከር ዲሞክራቲክ ኮንጓዊውን ሱሌይማን ሎኩዋን ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን ሌላው አዲስ ፈራሚ የኋላሸት ፍቃዱም የአጥቂ መስመር ተጫዋች ነው።

ከሁለቱ አጥቂዎች በተጨማሪ ግብ ጠባቂው ኢስማኤል ዋቴንጋ ፣ የመሀል ተከላካዩ ክሪዚስቶም ንታንቢ እና አማካዩ ካሉሻ አልሀሰንን በስብስቡ ውስጥ ያካተተው ኢትዮጵያ ቡና መያዝ የሚችለውን የውጪ ተጫዋቾች ኮታ ሙሉ ለሙሉ ተጠቅሟል።