ኢትዮጵያ ቡና የሦስት ተጫዋቾቹን ውል አራዝሟል

ኢትዮጵያ ቡና ለሦስት ወጣት ተጫዋቾቹ  የደሞዝ ማሻሻያ በማድረግ ለተጨማሪ ዓመት ውላቸውን ሲያራዝም ከሌሎች ሁለት ተጫዋቾች ጋር ደግሞ ድርድር ላይ ነው።

በ2010 የውድድር ዘመን በሊጉ ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ ያጠናቀቀዉ በአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ የሚመራው ኢትዮጵያ ቡና መልካም እንቅስቃሴ ላደረጉት ሦስት ወጣት ተጫዋቾቹ አቡበከር ነስሩ ፣ ሚኪያስ መኮንን እና ኃይሌ ገብረትንሳይ የደሞዝ ማሻሻያ በማድረግ ለተጨማሪ ሁለት ዓመታት በክለቡ የሚያቆያቸውን ውል አራዝሟል።

በ2009 በሐረር ሲቲ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ውስጥ የነበረው አቡበከር ነስሩ ኢትዮጵያ ቡናን ከተቀላቀለ በኋላ በፍጥነት ወደ ዋናው ቡድን ሰብሮ መግባት ችሏል። በተለይ አምና በሁለተኛው ዙር የመሰለፍ ዕድል ባገኘባቸው አጋጣሚዎች በአጠቃላይ 5 ጎሎች ማስቆጠር ችሏል ። በ2010 የመጀመርያ የውድድር ሳምንታት እምብዛም የመሰለፍ ዕድል ባያገኝም አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ ኢትዮጵያ ቡናን ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ ዕድል የተሰጠው ሲሆን ወጣቱ አጥቂ በሊጉ ሦስት ጎሎችን በስሙ አስመዝግቧል። በ2011 የአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ በሦስት ጎሎች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ የሆነው አቡበከር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ቀሪ የሁለት ዓመት ኮንትራት ቢኖረውም የክለቡ የረጅም ጊዜ ዕቅድ አካል መሆኑን በሚጠቁም መልኩ ተጨማሪ ሁለት ዓመታትን በመጨመር ለአራት ዓመታት የሚያቆየውን ፊርማ አጠናቋል። አቡበከር ከ17 ዓመት እና ከ20 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን መጫወት የቻለ ሲሆን በቅርቡ ለዋናው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ተጠርቶ በጉዳት ምክንያት ከስብስቡ ውጪ መሆኑ ይታወሳል።

ሌላኛው አጥቂ ሚኪያስ መኮንን እንደ አቡበከር ሁሉ ከሐረር ሲቲ 17 ዓመት በታች ቡድን ነበር በ2009 ኢትዮጽያ ቡናን የተቀላቀለው። በቴክኒክ ችሎታው የሚታወቀው ተጫዋቹ ሚኪያስ መኮንን ባለፉት ሁለት ዓመታት በተጫወተባቸው ጨዋታዎች ሁሉ ጉልበት በሚጠይቀው ሊግ ውስጥ በአዕምሮው በመጫወት ክህሎቱን እያሳየ ሲገኝ ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የሚያቆይባቸው ቀሪ ሁለት ዓመታት ቢኖሩም ለሌሎች ሁለት ዓመታት ውሉን በማራዘም የደሞዝ ማሻሻያ ተደርጎለት ለአራት ዓመታት ከክለቡ ጋር እንደሚዘልቅ ታውቋል።

ሦስተኛው ወጣት ተጫዋች የመስመር ተከላካዩ ኃይሌ ገ/ትንሳይ ከተስፋ ቡድን ነበር በ2010 ሁለተኛው ዙር ወደ ዋናው ቡድን ማደግ የቻለው። አብዱልከሪም መሀመድ ከኢትዮጵያ ቡና መልቀቁን ተከትሎ በቀኝ መስመር የተከላካይ ቦታ ላይ የተፈጠረውን ክፍተት እንዲሞላ በአሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜስ እምነት ተጥሎበት ነበር እንዲያድግ የተደረገው። በተሰለፈባቸው ጨዋታዎች ጥሩ ብቃቱን ማሳየት የቻለው ኃይሌ እንደ ሚኪያስ እና አቡበከር ሁሉ ቀሪ ሁለት ዓመት ኮንትራት ቢቀረውም የደሞዝ ማሻሻያ ተደርጎለት እና የሁለት ዓመት ውል ተጨምሮለት ከኢትዮዽያ ቡና ጋር የሚያቆየውን ውል ፈርሟል።

በተያያዘ ዜና ከኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን አንስቶ በዋናው ቡድን በመጫወት አምበል እስከመሆን የደረሰው አማኑኤል ዮሐንስ ምንም እንኳ ከቡድኑ ጋር የሚያቆየው ቀሪ ሁለት ዓመት ኮንትራት ቢኖረውም የሰጠውን መልካም አገልግሎት ከግምት በማስገባት ተጨማሪ አንድ ዓመት ከኢትዮዽያ ቡና ጋር ለመቆየት እየተደራደረ መሆኑ ታውቋል። ከ2007 መጨረሻ አንስቶ ከሀላባ ከተማ ኢትዮዽያ ቡናን በመቀላቀል ለተከታታይ ሦስት ዓመታት በተለያዩ አማራጭ ቦታዎች በመጫወት ወጥ የሆነ አቋም በማሳየት በደጋፊው ልብ ውስጥ መግባት የቻለው እያሱ ታምሩም እንደ አማኑኤል ዮሐንስ ሁሉ የአንድ ዓመት ኮንትራት ቀሪ ቢኖረውም ከደሞዝ ጭማሪ ጋር አንድ ዓመት በመጨመር ከክለቡ ጋር የሚያቆየውን አዲስ ኮንትራት ለመፈራረም ከአመራሮች ጋር እየተደራደረ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።