አዳማ ከተማ የሁለት ተጫዋቾችን ዝውውር አጠናቋል

በጅማ አባ ቡና ጥሩ የውድድር ዘመን ያሳለፉት ብዙዓየሁ እንደሻው እና ሱራፌል ጌታቸው የአዳማ ከተማ ዝውውራቸውን አጠናቀዋል። ሁለቱ ተጫዋቾች ወደ አዳማ ቀደም ብለው በማምራት የቡድኑ የቅድመ ውድድር ዝግጅት አካል የነበሩ ቢሆንም ከጅማ ጋር ያላቸውን ውል በስምምነት በማፍረስ መልቀቂያቸውን ባለመውሰዳቸው ምክንያት በይፋ መቀላቀል አልቻሉም ነበር።

በከፍተኛ ሊጉ በ20 ግቦች ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ ያጠናቀቀው ብዙዓየሁ ክለቡ ጅማ አባ ቡና በመጨረሻ በሽረ እንዳሥላሴ ተሸንፎ ወደ ፕሪምየር ሊጉ የመመለስ ውጥኑ ባይሳካም እዚህ ደረጃ ለመድረሱ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል። የቀድሞው የሐረር ቢራ እና ደደቢት አጥቂ የውል ማፍረሳ በመክፈል ከጅማ ጋር ተለያይቶ ለአዳማ ከተማ በሁለት ዓመት ውል የፈረመ ሲሆን የቡድኑን የጎል ማስቆጠር አቅም ያሳድጋል ተብሎ ይጠበቃል።

ሌላኛው የጅማ አባ ቡና የመሀል ሜዳ ተጫዋች ሱራፌል ጌታቸው ለጅማ አባቡና በመጀመሪያ ዓመቱ ወጥ አቋም በማሳየት ጎልተው ከታዩ ተጫዋቾች መካከል የሚጠቀስ ነው። ከሙገር ሲሚንቶ የተገኘው ሱራፌል እንደ ብዙዓየሁ ሁሉ በጅማ አባ ቡና የነበረውን የአንድ ዓመት ቀሪ ውል ማፍረሻ በመክፈል ተለያይቶ ነው ወደ አዳማ በሁለት ዓመት ኮንትራት ያመራው።

በክረምቱ በርካታ ተጫዋች ያስፈረመው አዳማ ከተማ ለሁለቱ ተጫዋቾች በድምሩ 800,000 (ስምንት መቶ ሺ ) የውል ማፍረሻ ለመክፈል መስማማቱ ታውቋል።


ማስታወቂያ
የኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ የዋናው እግርኳስ ቡድን የሚያደርጋቸውን ጨዋታዎች የቪድዮ ቀረጻ እና የጨዋታ ትንተና የሚያደርግ ባለሙያ ይፈልጋል፡፡ ስለሆነም በዚህ ሙያ ላይ የተሰማሩ አካላት በስራው ላይ ያላቸውን የታደሰ ህጋዊ ፍቃድ በመያዝ ሜክሲኮ በሚገኘው የክለቡ ጽህፈት ቤት በአካል በመቅረብ የፍላጎት ማሳወቂያ እና የመወዳደርያ ሰነድ መውሰድ የምትችሉ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

ለተጨማሪ መረጃ – 0115-534949 ; 0115-532051

ኢትዮ ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ