በዩኤፋ እና ካፍ በጋራ ያዘጋጁት የአቅም ግንባታ ስልጠና ተጀመረ

ለአምስት ቀናት የሚቆየው እና የ14 የአፍሪካ ሀገራት እግርኳስ ፌዴሬሽኖች ዋና ፀሀፊዎች የሚካፈሉበት የአቅም ግንባታ ስልጠና ዛሬ በካፒታል ሆቴል ተጀመረ።

የአፍሪካ እና የአውሮፓ እግርኳስ ማህበራት በጋራ በመሆን ያዘጋጁት ስልጠና ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን 14 የአፍሪካ ሀገራት ዋና ፀሀፊዎችን ተሳታፊ ያደርጋል። ስልጠናው በዋናነት ዓላማው ያደረገው የአፍሪካ ሀገራት ፌዴሬሽኖች ዋና ፀሀፊዎች የስፖርት አስተዳደር አቅማቸውን ማሳደግ ሲሆን ቀጣይነት ያለው እንደሆነም ተነግሯል ።

በስልጠናው ጅማሮ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝደንት አቶ ኢሳያስ ጂራ በመክፈቻ ንግግራቸው ‘እንኳን ደህና መጣችሁ’ ካሉ በኋላ ካፍ እና ዩኤፋ እንደነዚህ ያሉ የእግርኳስ አመራሮችን አቅም የሚያሳድግ እና ፌዴሬሽኖች ተቋማዊ የአደረጃጀት ለውጥ እንዲያመጡ የሚያግዝ ሥልጠና ማዘጋጀታቸውን አድንቀው ስልጠናው ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰጥ ስለመደረጉ አመስግነዋል። ፕሬዝዳንቱ እንግዶቹ በአምስቱ ቀናት እግረ መንገዳቸውን በአዲስ አበባ የሚገኙ የቱሪስት መስህብ ቦታዎችን እንዲጎበኙም ጥሪ አስተላልፈዋል።

በአፍሪካ በአራት ምድብ ተከፍሎ በተመረጡ አራት ሀገራት በሚሰጠው በዚህ የመጀመርያ ዙር ስልጠና የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽንን በመወከል አቶ ሰለሞን ገብረሦላሴ ተሳታፊ ሲሆኑ ሴካፋን ላለፉት አስራ አምስት ዓመታት በብቸኝነት በዋና ፀሀፊነት የመሩት እና ለተቋሙ ዕድገትም ሆነ መዳከም ተወቃሽም ተመስጋኝም የሆኑት ኬንያዊው ኒኮላስ ሙሶንዬም ስልጠናውን ከሚካፈሉ አካላት መካከል አንዱ ናቸው።