ደደቢት እግርኳስ ክለብ ለፌዴሬሽኑ አቤቱታውን አቀረበ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት ትግራይ ስታድየም ላይ በደደቢት እና ኢትዮጵያ ቡና መካከል የተካሄደው ጨዋታ “ያለ ክለባችን ፍቃድና እውቅና ውጭ የቀጥታ የሬዲዮ ስርጭት ተካሂዷል።” ሲል ለፌዴሬሽኑ አቤቱታውን አቀረበ።

” የደደቢት እግርኳስ ክለብ ጥቅምት 25 ቀን 2011 ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ባከናወነው ጨዋታ ላይ የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሀን (ኤፍኤም 96, 3) የሬዲዮ ጣቢያ ከእኛም ሆነ ከፌዴሬሽኑ ምንም አይነት ፈቃድና እውቅና ውጭ ጨዋታውን ማስተላለፉ ተገቢ አይደለም። ይህ በመሆኑ ክለቡ በዕለቱ የሜዳ ገቢ ላይ ኪሳራ ያደረሰ ከመሆኑም ባሻገር የህግ ጥሰት ተፈፅሟል።” በማለት በደብዳቤው ገልጾ ፌዴሬሽኑ የተፈፀመውን የህግ ጥሰት እና የደረሰውን ጉዳት ከግምት ውስጥ በማስገባት እርምጃ እንዲወስድ አቤቱታውን አቅርቧል። ደደቢት የመገናኛ ብዙሀን ለሀገራችን እግርኳስ እድገት እያበረከቱት ያለው አስተዋፆኦ ከፍተኛ መሆኑንም አያይዞ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ2011 የውድድር ዘመን ጨዋታዎችን ከፌዴሬሽኑ ፈቃድ ውጭ ማስተላለፍ እንደማይቻል በደብዳቤ ትዕዛዝ ማስተላለፉ ይታወቃል።