ዋልያዎቹ ለጋናው ጨዋታ ልምምድ ጀመሩ

ለ2019 የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ማጣርያ እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ኅዳር 9 ከጋና ጋር በአዲስ አበባ ስታድየም ለሚያደርገው 4ኛ የምድብ ጨዋታው የሚረዳውን ዝግጅት ጀመረ።

በአሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ መሪነት ባሳለፍነው አርብ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ ያደረገው ብሔራዊ ቡድኑ ከኢትዮዽያ ውጭ ከሚገኙት አራቱ ተጫዋቾች (ሽመልስ በቀለ ፣ ዑመድ ኡኩሪ ፣ ጋቶች ፓኖም እና ቢኒያም በላይ) በቀር 19 የቡድኑ አባላት ዛሬ ከ10:30 ጀምሮ በሱሉልታ በሚገኘው ያያ ቪሌጅ ሜዳ በመገኘት ከኳስ ጋር የተያያዙ ቀለል ያሉ ልምምዶች ሰርተዋል።


በዛሬው ልምምድ በኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን ለመጀመርያ ጊዜ ጥሪ የተደረገላቸው ዳንኤል ደምሴ እና አበበ ጥላሁን ሲገኙ የፈረሰኞቹ እና የብሔራዊ ቡድን አንበል ጌታነህ ከበደ ባጋጠመው መጠነኛ ጉዳት የተነሳ ከህክምና ባለሙያው ይስሀቅ ሽፈራው በሚሰጠው ሙያዊ ድጋፍ ከቡድኑ ተነጥሎ ቀለል ያሉ ልምድዶችን ሰርቷል።

ቡድኑ ከዛሬ ጀምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት ከፍተኛ ቦታ ላይ በሚገኘው ሱሉልታ ያያ ቪሌጅ ልምምዱን በመስራት ይቀጥልና እስከ ጨዋታው መዳረሻ ድረስ በአዲስ አበባ ስታድየም የሚያደርግ ይሆናል።ኅዳር 9 በአዲስ አበባ ስቴዲየም የሚደረገውን ጨዋታ ደቡብ አፍሪካዊው ዳኛ ቪክቶር ሚጉዌል ጎሜዝ የሚመራው ይሆናል።