አንድ ኢትዮጵያዊ ተጫዋች ለሙከራ ወደ ግብፅ ያመራል

ከኢትዮጵያ ቡና ተስፋ ቡድን የተገኘው የቀድሞው የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች እሱባለው ጌታቸው ለሙከራ ወደ ግብፅ እንደሚሄድ ታውቋል።

ከ2007 ጀምሮ በኢትዮጵያ ቡና ከ17 ዓመት በታች ቡድን በመጫወት ያሳለፈው እና ማዳጋስካር አዘጋጅታው በነበረው የአፍሪካ ከ17 ዓመት በታች ዋንጫ ኢትዮጵያ ሁለት የደርሶ መልስ የማጣሪያ ጨዋታዎችን ከግብፅ እና ከማሊ ጋር ስትጫወት በአሰልጣኝ አጥናፉ ዓለሙ ዕምነት ተጥሎበት በአማካይ ስፍራ ላይ በሁሉም የማጣርያ ጨዋታዎች ተሰላፊ በመሆን አቅሙን ያሳየው እሱባለው ጌታቸው ለሙከራ ወደ ግብፅ ሊያመራ ነው።

እሱባለው ከብሔራዊ ቡድን መልስ ከ2009 ጀምሮ ወደ ዋናው የቡናማዎቹ ቡድን በማደግ ተቀይሮ በመግባት ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያደረገ ሲሆን 2010 ላይ በልምምድ ወቅት ባጋጠመው ጉዳት ለአራት ወራት ከሜዳ ከራቀ በኋላ በፍጥነት ወደ ሜዳ ሳይመለስ በመቅረቱ የተነሳ ወደ ትክክለኛ አቋሙ ሳይመለስ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ዘንድሮ ተለያይቷል።

ተጫዋቹ ምንም እንኳን ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ቢለያይም አሁን ከጉዳቱ አገግሞ በመመለሱ የጋቶች ፓኖም ህጋዊ ወኪል የሆነው ዴቪድ በሻህ የግብፅ ሙከራው ዕድል አግኝቶለታል። ለጊዜው የሚሄድበት ክለብ ስም ባይታወቅም የግብፅ ሁለተኛ ሊግ ቡድን ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል። እሱባለው ሰሞኑን በኢትዮጵያ የሚገኘው የግብፅ ኤምባሲ ቪዛ ከመታለት በኋላ ወደ ግብፅ የሚያቀና ይሆናል።

ምንም እንኳ የተሳካ ባይሆንም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያዊያን ተጫዋቾች የሆኑት ሚኪያስ መኮንን ፣ ጫላ ተሺታ (ቱኒዚያ) ፣ ሙጂብ ቃሲም (ሞሮኮ) ፣ ሚኪያስ ግርማ (ታይላንድ) ፣ ከነዓን ማርክነህ (ሰርቢያ) በመሄድ ሙከራ ጊዜ አሳልፈው መምጣታቸው ይታወቃል።