አዳማ ከተማ ከግብ ጠባቂው ጋር ሊለያይ ነው

በስብስቡ ውስጥ አራት ግብ ጠባቂዎችን የያዘው አዳማ ከተማ ያለፉትን ስድስት ዓመታት ከታዳጊ ቡድኑ ጀምሮ በግብ ጠባቂነት ሲያገለገል ከነበረው ጃፋር ደሊል ጋር በስምምነት ሊለያይ ተቃርቧል።  

ከሦስት ጨዋታዎች ሙሉ ሦስት ነጥብ ማሳካት ያልቻለው አዳማ ከተማ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ባልተጠበቀ ሁኔታ ዩጋንዳዊው ግዙፍ ግብጠባቂ ሮበርት ኦንዶካራን ማስፈረሙ ይታወቃል። የሮበርት ለአዳማ መፈረምን ተከትሎ ላለፉት ሶስት ዓመታት በክለቡ ውስጥ የሚገኘው ዲሞክራቲክ ኮንጓዊው ጃኮ ፔንዜ ከአዳማ ጋር ይለያያል ተብሎ ቢጠበቅም የመቆየቱ ነገር እርግጥ ሆኗል። በዚህም ምክንያት አዳማ ከተማ ከሁለቱ የውጪ ዜጎች በተጨማሪ ዳንኤል ተሾመ እና ጃፋር ደሊልን በስብስቡ ይዟል።

ከክለቡ እንደወጣ መረጃ ከሆነ በስብስቡ ውስጥ አራት ግብ ጠባቂዎችን በአረንጓዴ መታወቂያ ይዞ መቀጠል የማይችል በመሆኑ አንድ ግብ ጠባቂ የመቀነስ ግዴታ ውስጥ ገብቷል። በዚህም ያለፉትን ስድስት ዓመታት በክለቡ የቆየውና በ2007 አዳማ ከተማ ወደ ፕሪምየር ሊጉ እንዲመለስ ካስቻሉ ተጫዋቾት አንዱ ከሆነው ጃፋር ደሊል ጋር በስምምነት ሊለያይ እንደሆነ ተሰምቷል። ጃፋር በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት በተጠባባቂ ወንበር ላይ በመቀመጥ እና በጥቂት አጋጣሚዎች የመጀመርያ ተሰላፊ በመሆን ሲያገለግል የቆየ ሲሆን በስምምነቱ መሰረት የውድድር ዘመኑ አጋማሽ የተጫዋቾች ዝውውር መስኮት ሲከፈት ወደፈለገበት ክለብ ሊያመራ እንደሚችል ተነግሯል።

በሊጉ ኢትዮጵያውያን ግብ ጠባቂዎች እየመነመኑ ባሉበት በዚህ ወቅት አዳማ ከተማ ሁለት የውጭ ዜግነት ያላቸው ግብጠባቂዎችን በስብስቡ ያካተተ የመጀመርያው ክለብ አድርጎታል።