የአሰልጣኞች አስተያየት| ኢትዮጵያ ቡና 1-1 ወላይታ ድቻ

አምስተኛው ሳምንት የኢትየጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዛሬ ቀጥሎ ሲካሄድ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ ኢትዮጵያ ቡና እና ወላይታ ድቻ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ ውጤት ተጠናቋል፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኃላ የሁለቱ ቡድን አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡


“አቻ መውጣት አይገባንም ነበር”- ዲዲየ ጎሜዝ (ኢትዮጵያ ቡና)

ስለ ጨዋታው…

” ጨዋታው ጥሩ የሚባል ነበር ፤ ሙሉ የጨዋታውን ክፍለ ጊዜ ብልጫ ወስደን መጫወት ችለናል፡፡ በአጠቃላይ ስናየው መጥፎ ጨዋታ አልነበረም ነገርግን በውጤቱ በእጅጉ ተከፍተናል፡፡ በጨዋታው አቻ መውጣት አይገባንም ነበር በተቻለን መልኩ አጥቅተን ለመጫወት ሞክረናል፡፡በጣም ከሚከላከለው ወላይታ ድቻ ጋር ተጫውተን 2 ነጥብ በማጣታችን አዝኛለሁ፡፡ስታዲየም ሙሉ የነበረው ደጋፊያችንን ማመስገን እፈልጋለሁ ፤ እንደእኛው በውጤቱ ቢከፋም በጎ መንፈሱ አሁንም እንዲቀጥል እንፈልጋለን፡፡”

ስለ ወላይታ ድቻ…

” መጫወት የሚፈልጉትን የመከላከል እግርኳስ በጥሩ መልኩ መከወን ችለዋል፡፡ለተጫዋቾቼ ከጨዋታው በፊት እደነገርኳቸው በመልሶ ማጥቃቱም አደገኞች ነበሩ። በመጀመሪያው አጋማሽ 3 አደገኛ የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎችን አግኝተው ነበር። ነገርግን በሁለተኛው አጋማሽ ያንን መቆጣጠር ችለን ነበር። በጥቅሉ መጥፎ የሚባል ቡድን አይደለም፡፡”


“ከሜዳ ውጪ ከኢትዮጵያ ቡና አንድ ነጥብ ይዞ መመለስ ለእኛ ትልቅ ውጤት ነው፡፡”- ዘነበ ፍሰሃ ( ወላይታ ድቻ)

ስለ ጨዋታው…

“ከሜዳችን ውጪ የተደረገ ጨዋታ እንደመሆኑ በተቻለን መጠን ተጠንቅቀን ለመጫወት ሞክረናል። ይህ ጥንቃቄያችን ግን ለዘጠና ደቂቃ መዝለቅ ባለመቻሉ ግብ አስተናግናል። ከሞላ ጎደል ቡና ከኛ በተሻለ ተጭኖ ለመጫወት ሞክሯል ከሜዳ ውጪ ከኢትዮጵያ ቡና አንድ ነጥብ ይዞ መመለስ ለእኛ ትልቅ ውጤት ነው፡፡”

ስለጨዋታው ኮከብ…

“በዛሬው ጨዋታ ለእኔ መሀል ሜዳ ላይ የነበረው በረከት ወልዴ እጅግ ድንቅ ነበር። እሱ ከዕድሜው በላይ ነው እየተጫወተ የሚገኘው። ከእሱ በተጨማሪ አምና ከ17 አመት በታች ቡድናችን ያሳደግናቸው 3 ተጫዋቾችም ጥሩ ነበሩ፡፡”