የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የእጣ ማውጣት ስነ-ስርአት ዛሬ ተካሄደ

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የ2010 የውድድር ዘመን አፈፃፀምና 19 ክለቦች ተሳታፊ የሚሆኑበት የ2011 የውድድር ዘመን እጣ የማውጣት ስነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት በኢትዮጵያ ሆቴል ተካሂዷል፡፡

የፊዴሬሽኑ ሞክትል ፕሬዝዳንት የሆኑት ኮሎኔል ዐወል አብዱራሂም እንዲሁም ጊዜያዊ የፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት የተካሄደውን የዛሬውን መርሐ ግብር በመክፈቻ ንግግር የከፈቱት ኮሎኔል አወል አቡዱራሂም በፌዴሬሽኑ ስር እየተካሄዱ ካሉት ውድድሮች መካከል እጅግ ወሳኙ ውድድር ይህ እና ከዚህ በታች ያለው ከ17 ዓመት በታች የሊግ ውድድር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ በቀጣይም አሁን ላይ ያለውን የእግርኳሳችን የሜዳ ላይ ችግሮችን ለመቅረፍ በቀጣይ ከሁለቱ የእድሜ እርከን ውድድሮች በተጨማሪ ሌሎች ተመሳሳይ የእድሜ እርከን ውድድሮችን ለመጀመርና የእግርኳስ ልማቱን እስከ ሠፈሮች ድረስ በመድረስ ወደፊት የተሻሉ ስፖርተኞችን ለማውጣት አዲሱ ፌዴሬሽን በቁርጠኝነት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡

በቀጣይም የፌዴሪሽኑ የህክምና ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዘሪሁን ቀቀቦ በተጫዋቾች የእድሜ ተገቢነትና ኤምአራአይ ምርመራ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ዘሪሁን በንግግራቸው እንደገለፁት የአፍሪካ ሐገር እንደመሆናችን በአንፃራዊነት በእድሜ ተቀራራቢ የሆኑ ተጫዋቾች እንዲወዳደሩ ከማድረግ በዘለለ እንደሌሎች የአውሮፓ ሐገራት ከእድሜ ማጭበርበር የፀዳ ውድድር ለማካሂድ ብዙ ስራ እንዲጠይቅ ተናገረዋል ፤ በተቻለ መጠን ይህንን ችግር ለመቅረፍ ፌዴሬሽኑ ከክለቦች ጋር በመሆን ከኤምአርአይ ምርመራው በተጨማሪ ከክለቦች ጋር በመተባባር ዲጂታል ስርዓትን ለመጀመር እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡

በማስከተልም የውድድሩ ከፍተኛ ባለሙያ በሆኑት በአቶ ዳንኤል ዘለቀ የ2010 ዓ.ም የU-20 ፕሪምየር ሊግ ውድድር አፈፃፀም ሪፖርት ቀርቧል፤ ከቀረበው ሪፖርት ትኩረት የሚስበው ዐቢይ ጉዳይ የነበረው በአጠቃላይ በአመቱ ከተካሂዱ 240 ጨዋታዎች ላይ የተመዘዙት 7 ቀይ ካርድ ብቻ መሆናቸው በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል የሚገባ የሚያበረታታ ጉዳይ ሆኖ አልፏል፡፡

ፕሮግራሙ ከሻይ እረፍት ሲመለስ የሊግ ኮሚቴ አባልና የውድድሩ ምክትል ሰብሳቢ በሆኑት ኢንስፔክተር ጌታቸው የማነብርሃን ስለተሻሻሉት የውድድር ደንብ አንቀጾች ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል። በዚህም መሠረት ከዘንድሮ የውድድር ዘመን አንስቶ የሀዘንና የህሊና ፀሎት የሚደረግላቸው ከስፓርቱ ጋር ግንኙነት ያላቸውና ተሳታፊ የነበሩት አካላት የቀብር ስነ-ስርአታቸው ከተፈፀመ በኃላ እንዲሆን ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ሌላው የተሻሻለው የውድድር ደንብ መሠረት ሁለት ቡድኖች በነጥብም በግብ ልዩነትም እኩል ሆነው ሲገኙ በተጨማሪም የውድድሩ ይዘት የዙር እንደመሆኑ በዙር ውድድር ሁለቱም አንድ አንድ ጊዜ መሸናነፍ ቢችሉም አሸናፊውን ቡድን በሁለቱ ዙሮዎች ባስመዘገበው የስፓርታዊ ጨዋነት  ድምር ውጤት የተሻለ ነጥብ ያገኘው ቡድን አሸናፊ የሚሆን ይሆናል የሚል አንቀፅ በአዲስ መልኩ ወደ ውድድሩ ደንብ ውስጥ ተካቷል፡፡

በውድድሩ ደንብ ዙሪያ ከተሳታፊ ክለቦች የተለያዩ ጥያቄዎች የተነሱ ሲሆን በተለይም የወላይታ ድቻው ተወካይ የሆኑት አቶ ዘላለም ማቴዎስ ከክልል ለሚመጡ ክለቦች በተለይም አዲስአበባ ጨዋታ ኖሯቸው በሚመጡበት ወቅት ምቹ የሆነ የመለማመጃ ሜዳን ለማግኘት አዳጋች እንደሚሆንባቸውና የትራንስፖርት አቅርቦት ያላመቻቸ ክለብ እስከ ነጥብ የሚደርስ ቅጣት ይኖራል መባሉን ክለቦች ከዋናው ቡድን በሚተርፉ መጠቀሚያዎች እንደመጠቀማቸው ይሄንን እውነታ እንዴት ማስታረቅ ይቻላል የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡

በተነሳው ጥያቄ ላይ ምላሻቸውን የሰጡት ኢንስፔክተር ጌታቸው ሲመልሱ እንዳሉት ከሆነ ይህን ጉዳይ መነሳት ያስፈለገው በተለይ አንዳንድ የአዲስአበባ ክለቦች የራሳቸው የሆነ ሜዳ እያላቸው ፍቃደኛ ባለመሆን የውድድር ሂደቶች ላይ ሳንካን እየፈጠሩ ስለሚገኝና በደንቡ መሠረት ባለሜዳው ቡድን ይህንና መሠል ጉዳዮችን ማሟላት ግዴታ አለበት ፤ ይህንን ያለከበረ ቡድን በደንቡ መሠረት ቅጣት ይጠብቀዋል ብለዋል ። በተጨማሪም አብዛኞቹ ቡድኖች ከክልል ሲመጡ አብዛኛዎቹ የራሳቸውን ትራንስፖርት ይዘው ይመጣሉ፤ ይህ በማይሆንበት ሁኔታ ላይ ግን ባለሜዳው ክለብ አቀርባለው ብሎ ከተስማማ በኃላ ሳያቀርብ ከተገኘ ግን ቅጣት ይጠብቀዋል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከዕጣ ማውጣቱ ስነ-ስርዓት በፊት አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ለተሳታፊ ክለቦች አጠቃላይ ትኩረት ሊሰጧቸው በሚገቡ ወሳኝ ነጥቦች ዙርያ መጠነኛ መግለጫ ሰጥተዋል። በዚህም ወቅት ከተሳታፊዎች በተነሳ ጥያቄ መሠረት የውድድሩ ጅማሮ ጊዜ ከነበረበት ታኅሳህ 13 ወደ ታህሳስ 20 እና 21 እንዲሸጋገር ከስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡

በመጨረሻም አምና በ15 ክለቦች መካከል የተካሄደውና ዘንድሮ ደግሞ በ19 ክለቦች መካከል የሚካሄደው ውድድር የእጣ ማውጣት ስነስርአት ተካሂዷል። በዚህም መሠረት አምና ይካፈሉ ከነበሩት ክለቦች መካከል ደደቢት ስፖርት ክለብ ቡድኑን በማፍረሱ የተነሳ በውድድሩ የማይካፈል ሲሆን በተቃራኒው ደግሞ 5 ክለቦች ደግሞ አዳዲስ ተሳታፊዎች ሆነው ወደ ውድድሩ የሚገቡ ይሆናል፡፡ እነዚህም ፋሲል ከነማ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ሀላባ ከተማ ፣ አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽንና አምቦ ጎል ፕሮጀክት አዳዲስ የውድድሩ ተሳታፊ ክለቦች ናቸው፡፡

በሁለት ምድቦች ተከፍሎ የሚከናወነው ይህ ውድድር ቡድኖቹ በሚከተለው መልኩ ተደልድለዋል፡፡

ምድብ ሀ

ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ ኢትዮ/ወ/ስ አካዳሚ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ ወላይታ ድቻ፣ ሲዳማ ቡና ፣ ሀዋሳ ከተማ፣ አምቦ ጎል ፕሮጀክት፣ ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ፣ ድሬዳዋ ከተማ 

ምድብ ለ

አፍሮ ጽዮን ኮንስትራክሽን፣ ኢትዮጵያ መድን፣ አዲስ አበባ ከተማ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ወልቂጤ ከተማ፣ ሀላባ ከተማ፣ አዳማ ከተማ፣ ጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ፣ ፋሲል ከነማ 

የምድብ ሀ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ-ግብር

(ታኅሳስ 20 እና 21 ቀን 2011)

ኢትዮጵያ ቡና ከ ኢትዮ/ወ/ስ አካዳሚ

ጥሩነሽ ዲባባ ከ ወላይታ ድቻ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ አምቦ ጎል ፕሮጀክት 

መከላከያ ከ ሀዋሳ ከተማ

ሲዳማ ቡና ከ ድሬዳዋ ከተማ

የምድብ ለ የመጀመሪያ ሳምንት መርሐ-ግብር

(ታኅሳስ 20 እና 21 ቀን 2011)

ወልቂጤ ከተማ  ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ 

ጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ  ከ አዳማ ከተማ

ኢትዮጵያ መድን ከ ሀላባ ከተማ

አፍሮ ጽዮን ከ ፋሲል ከነማ

*አዲስ አበባ ከተማ በመጀመሪያው ሳምንት አራፊ ይሆናል 

የዓመቱ የምድብ ውድድር ሲጠናቀቅ ከየምድቡ ከአንድ እስከ ስድስት የወጡ ቡድኖች እንደከዚህ ቀደሙ በተመረጠ ከተማ የማጠቃለያ ውድድር ያካሂዳሉ።