ሴቶች አንደኛ ዲቪዝዮን | ንግድ ባንክ ጥረትን አሸንፏል

የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ አንደኛ ዲቪዝዮን ሰባተኛ ሳምንት ዛሬ በተደረገ አንድ ጨዋታ ሲጀመር ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሜዳው ጥረትን 1-0 አሸንፏል።

08:00 በአዲስ አበባ ስታድየም በተደረገው ጨዋታ የመጀመርያው አጋማሽ ብዙም ማራኪ ያልነበረ እና የሚቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ሆኖ ያለፈ ሲሆን ኳሱን ይዘው በይበልጥ በቀኝ መስመር ላይ ባጋደለ መልኩ የማጥቃት እንቅስቃሴ እና የጎል ዕድል በመፍጠር ረገድ ከጥረት ይልቅ ንግድ ባንኮች የተሻሉ ሆነዋል። ይሁን እንጂ ንግድ ባንኮች በመጀመርያው አርባ አምስት ጠንካራ የጎል እድል መፍጠር የቻሉት በሁለት አጋጣሚ ብቻ ነበር። 24ኛው ደቂቃ ላይ አጥቂዋ ረሂማ ዘርጋው ወደ ጎል የመታችው ኳስ ግብ ጠባቂዋን ታሪኳ በርገናን ቢያልፍም አሳቤ ሙሶ ከመስመሩ ሳያልፍ ጎል እንዳይሆን ያወጣችው እና ተቀይራ የገባችው የመስመር አጥቂዋ ታደለች አብርሃ 43ኛው ደቂቃ ከግራ መስመር አክራ የመታችውን የጥረቷ ግብ ጠባቂ ታሪኳ በርገና ያወጣችው ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ ። የጨዋታው ደቂቃ እየገፋ በሄደ ቁጥር እየተነቃቁ የመጡት ጥረቶች 34ኛው ደቂቃ ላይ የንግድ ባንኳ ተከላካይ ጥሩአንቺ መንገሻ የሰራችውን ስህተት ተጠቅማ የጥረቷ አጥቂ ምስር ኢብራሂም ነፃ የሆነ ኳስ አንድ ለአንድ ከግብጠባቂዋ ንግስቲ ጋር ተገናኝታ አገባችው ሲባል በሚገርም ብቃት ንግስቲ እንደምንም ያወጣችባት ኳስ የሚጠቀስ ብቸኛ ሙከራቸው ነው።

ከእረፍት መልስ ሙሉ ለሙሉ ተሽለው በመቅረብ ብልጫ የወሰዱት ንግድ ባንኮች የአማካይዋ ዙሌካ ጁሀድ ተቀይሮ መግባት በቡድኑ የማጥቃት እንቅስቃሴ ላይ ለውጥ የፈጠረ ሲሆን በርከት ያሉ የጎል ሙከራዎችን አድርገዋል። በዋናነት በሁለት አጋጣሚ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ያመራችው ብዙዓየሁ ታደሰ ጎል መሆን የሚችሉ ኳሶችን ሳትጠቀም የቀረችበት አጋጣሚ የሚያስቆጩ ናቸው። በዕለቱ በንግድ ባንክ በኩል ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው የመስመር አጥቂዋ ታሪኳ ደቢሶ ላይ የተሰራውን ጥፋት ተከትሎ 63ኛው ደቂቃ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ህይወት ደንጊሶ ወደ ጎልነት ቀይራው ንግድ ባንኮች መሪ ማድረግ ችላለች። ከጎሉ መቆጠር በኋላ ተጨማሪ ጎል መጠናቸውን ከፍ ማድረግ የሚችሉ አጋጣሚዎችን ያገኙ ሲሆን በተለይ ረሂማ ዘርጋው ከሽታዬ ሲሳይ ተጥሎላት የግቡን አቋሚ ታኮ የወጣው ኳስ ጎል መሆን የሚችል ነበር። በጥረቶች በኩል ምንም አይነት የጎል ሙከራም ሆነ ወደ ጨዋታው የሚመልሳቸውን የጎል አጋጣሚ መፍጠር ሳይችሉ ጨዋታው በንግድ ባንክ 1 – 0 በሆነ ጠባብ ውጤት ተጠናቋል። በዚህም ንግድ ባንኮች አዳማ ከተማ ነገ ጨዋታ እስኪያደርግ የሊጉን መሪነት መያዝ ችለዋል።

የሊጉ ሰባተኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገ ይቀጥላሉ

7ኛ ሳምንት
ቅዳሜ ታኅሳስ 27 ቀን 2011
ኢትዮ ንግድ ባንክ 1-0 ጥረት ኮርፖሬት
እሁድ ታኅሳስ 28 ቀን 2011
ቅዱስ ጊዮርጊስ 08:00 አዲስ አበባ ከተማ
ጌዴኦ ዲላ 09:00 ሀዋሳ ከተማ
ድሬዳዋ ከተማ 09:00 አዳማ ከተማ
አርባምንጭ ከተማ 09:00 ጥሩነሽ ዲባባ
ኢትዮ ኤሌክትሪክ 10:00 መከላከያ
_____

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *