U-20 ምድብ ለ | አዳማ በመሪነቱ ሲቀጥል ሀላባ ከሜዳው ውጪ አሸንፏል

የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የምድብ ለ 8ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ተካሂደው ተጠባቂው የአአ ከተማ እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በአቻ ውጤት ሲጠናቀቅ ሀላባ ከሜዳው ውጪ አሸንፏል።

ኒያላ ሜዳ ላይ አዲስ አበባ ከተማን ከ አዳማ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ 2-2 ተጠናቋል። አዳማ በዚህ ጨዋታ ማሸነፍ የሚችል ከሆነ የምድቡ መሪነቱን የሚያሰፋበት እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ ድል የሚቀናው ከሆነ አንድ ተስተካከይ ጨዋታ እየቀረው የምድቡ መሪ መሆን የሚችልበት ጨዋታ በመሆኑ ጠንካራ ፉክክር ይስተናገዳል ተብሎ የተጠበቀ ሲሆን እንደተገመተው ሁሉ ሜዳ ላይ የተመለከት ነው ፉክክር ይሄን የሚያሳይ ነበር።

የመጀመርያዎቹን አስር ደቂቃዎች በተሻለ ሁኔታ ይንቀሳቀሱ የነበሩት አዲስ አበባዎች በ4ኛው ደቂቃ በአምበላቸው ያብቃል ፈረጃ አማካኝነት ከሳጥን ውጭ የመታወን ግብጠባቂው በቃሉ አዱኛ ያወጣበት እንዲሁም 9ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻገረውን ተከለካዩ ዳዊት ሳህሌ በግንባሩ ገጭቶ የወጣበትኔ የጎል ዕድሎች ፈጥረዋል።

ምንም እንኳ የጨዋታው እንቅስቃሴው በመሀል ሜዳ ላይ የተገደበ ቢሆንም በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ተመልክተናል። እንግዶቹ አዳማዎች በ20ኛው ደቂቃ ቢንያም አይተን ያልተጠቀመመበት፣ 28ኛው ደቂቃ የአዲስ አበባ ተከላካዮችን በማለፍ ዮናስ አብነት ጎል መሆን የሚችል አጋጣሚዎችን ያመከነበት አዳማዎችን መሪ ማድረግ የሚችሉ ዕድሎች ነበሩ። ብዙም ሳይቆይ የአዲስ አበባ ተከላካዮች የአዳማው ዱራሽ ሹቢክ ከጨዋታ ውጭ አቋቋም መስሏቸው በተዘናጉበት ጊዜ ብቻው ከግብጠባቂው ጋር ተገናኝቶ በእግሮች መሐል አሾልኮ ለማስቆጠር ሲሞክር የወጣበት ኳስ የሚያስቆጭ ነበር። በተወሰነ መልኩ በእንቅስቃሴ በኩል ቀዝቀዝ እያለ በመሄዱ ጎልም የጎል ሙከራ ሳንመለከት ቀርቷል።

ከእረፍት መልስ አዲስ አበባዎች ወደ ፊት ተጭነው እየተጫወቱ ባለበት ጊዜ በ53ኛው ደቂቃ ከአማካዮቹ የተቀበለውን ኳስ በሚገባ ተቆጣጥሮ ብሩክ ሰሙ ጎል በማስቆጠር አዲስ አበባዎችን መሪ ማድረግ ቻለ። ጎሉን ካስቆጠሩ በኋላ በአጨዋወታቸው የተዳከሙት አዲስአበባዎች በተለይ በቡድኑ እንቅስቃሴ ውስጥ ጥሩ ሚና የነበረው አምበሉ ያብቃል እንቅስቃሴ መውረድ ተፅእኖ ሲያደርግባቸው ታይቷል።

ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ አዳማዎች የተጫዋች ቅያሪ በማድረግ በተሻለ መንቀሳቀስ የቻሉ ሲሆን 61ኛው ደቂቃ ዮናስ ዮሐንስ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ የመታው ኳስ ለጥቂት ኳሱ ረዝሞበት ከወጣበት ሙከራ በኋላ የጨዋታውን መንፈስ የቀየሩ ሁለት ጎሎች በአንድ ደቂቃ ልዩነት ተቆጥረዋል። 71ኛው ደቂቃ በጥሩ ቅብብል የገቡት አዳማዎች በዮናስ ዮሐንስ ጎል አቻ መሆን ሲችሉ በድጋሚ በ74ኛው ሳይጠበቅ በመልሶ ማጥቃት ቢንያም አይተን ጎል አስቆጥሮ አዳማዎችን መሪ ማድረግ ችሏል።

አዳማዎች መሪነታቸውን ማስፋት የሚችሉበትን እድል 78ኛው ደቂቃ አግኝተው ቢንያም አይተን ሳይጠቀምበት ቀርቷል። አልፎ አልፎ ወደ አዳማ የግብ ክልል ይደርሱ የነበሩት አዲስ አበባዎች 81ኛው ደቂቃ ኳስ በእጅ በመነካቱ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ብሩክ ሰሙ አስቆጥሮ አቻ መሆን ችለዋል። በቀሩት ደቂቃ አዳማዎች ተጭነው ቢጫወቱም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠር 2-2 በሆነ ውጤት ተጠናቋል።

ከአዲስ አበባ በኩል የመስመር አጥቂው ያብቃል ፈረጃ በአዳማ በኩል አማካዩ አላሚን ከድር ለወደፊቱ ተስፋ ያላቸው ተጫዋቾች መሆናችውን መመልከት ችለናል።
በዚህ ምድብ ዛሬ ሌሎች ሁለት ጨዋታዎች ተደርገው ወደ ወልቂጤ ያመራው ሀላባ ከተማ ወልቂጤ ከተማን 3-0 ሲያሸንፍ መድን ሜዳ ላይ ኢትዮጵያ መድን ከ አፍሮ ፅዮን ያደረጉት ጨዋታ 1-1 ተጠናቋል። አሰላ ኅብረት ከ ፋሲል ከነማ የሚያደርጉት ጨዋታ ነገ 8:00 አሰላ ላይ ሲደረግ ኤሌክትሪክ የዚህ ሳምንት የምድቡ አራፊ ቡድን ነው።

የምድብ ሀ 8ኛ ሳምንት መርሐ ግብር

ኢ/ወ/ስ አካዳሚ ከ ወላይታ ድቻ (4:00 አካዳሚ ሜዳ)
ኢትዮጵያ ቡና ከ አምቦ ጎል (7:00 አአ ስታድየም)
ጥሩነሽ ዲባባ አካዳሚ ከ ሀዋሳ ከተማ (9:00 አሰላ)
ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ድሬዳዋ ከተማ (8:00 ጊዮርጊስ ሜዳ)
መከላከያ ከ ሲዳማ ቡና (4:00 መከላከያ ሜዳ)


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *