አአ U-17 | ኢትዮጵያ መድን መሪነቱን ይዟል

የአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ከ17 ዓመት በታች ውድድር 8ኛ ሳምንት አምስት ጨዋታዎች ዛሬ ተካሂደው ኢ/ወ/ስ አካዳሚ፣ ኢትዮጵያ መድን እና አዳማ ከተማ ድል ሲቀናቸው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ጥሏል። የኢትዮጵያ ቡና እና ኤሌክትሪክ ጨዋታ ደግሞ በከባድ ዝናብ ተቋርጧል።

ሀሌታ ከአካዳሚ ያደረጉት ጨዋታ ጥሩ እንቅስቃሴ አስመልክቶን በአካዳሚ 6-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። በሀሌታ በኩል ኳሱን ተቆጣጥሮ በመጫወት ወደፊት ለመሄድ የሚያደርጉት ጥረት መልካም ቢሆንም የጎል ዕድል በመፍጠር ረገድ ውስንነቶች ነበሩ። አካዳሚ ፍጥነት ባላቸው የፊት መስመር አጥቂዎቹ አማካኝነት የሚሰነዝረው ጥቃት አደገኛ በመሆኑ በደቂቃዎች ልዩነት አጥቂው ከድር ዓሊ የግል ጥረቱን ተጠቅሞ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች አካዳሚ 2-0 እየመራ እረፍት ወጥተዋል።

ከእረፍት መልስ አካዳሚዎች በክፍት ጨዋታ መልካሙ የስጋት ሦስተኛ ጎል ሲያስቆጥሩ ከደቂቃዎች በኃላ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ወደ ጎል መቶ እና በጨዋታ ናትናኤል ኪሮስ አከታትሎ ሁለት ጎሎችን ማስቆጠር የግብ መጠናቸውን ወደ አምስት አሳድገዋል። በሀሌታዎች በኩል ማስተዛዘኛ ሊሆን የሚችል የጎል አጋጣሚ በፍ/ቅ/ምት ቢያገኙም ይስሐቅ መኩሪያ ሳይጠቀምበት ቀርቷል። በመጨረሻው ደቂቃ ለአካዳሚ ስድስተኛ ለራሱ ሐት-ትሪክ የሰራበትን የማሳረጊያ ጎል ከድር ዓሊ አስቆጥሯል።


ከድር በውድድሩ የከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትት በዘጠኝ ጎል እየተፎካከረ ይገኛል። በየጨዋታዎቹ አስገራሚ አቋሙን እያሳየ የሚገኘውና በዛሬው ጨዋታም ሦስት ጎሎችን በማስቆጠር ልዩነት እየፈጠረ የሚገኘው የአካዳሚው አጥቂ ከድር የኢትዮጵያ ወጣቶች አካዳሚ በእግርኳሱ ላይ ከፍተኛ ተስፋ የሚጣልባቸውን ታዳጊዎችን እያፈራ መሆኑን አንድ ማሳያ ሊሆን የሚችል ተጫዋች ነው።

05:00 የቀጠለውና የአፍሮ ፅዮን ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያካሄዱት ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት ተጠናቋል። ከዚህ ቀደም ከነበሩ ጨዋታዎቻቸው ዛሬ ደካማ እንቅስቃሴ ያሳዩት ፈረሰኞቹ በአፍሮ ፅዮን ተፈትነዋል። ተሻሽለው የቀረቡት አፍሮ ፅዮኖችም አሸናፊ አክመል ባስቆጠራት ጎል መምራት ችለዋል። የጎል ሙከራ በመፍጠር ረገድ ብዙ የተቸገሩት ጊዮርጊሶች በአፍሮ ፅዮን 1 – 0 እየተመሩ ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከእረፍት መልስ በጨዋታው እንቅስቃሴ አንድ የፈጠሩትን የግብ ዕድል ከርቀት በሚገርም ሁኔታ ፉአድ ሀቢብ ጎል አስቆጥረው አንድ አቻ መሆን ችለዋል። በዳኝነት በኩል መሠረታዊ የሚባሉ የህግ ጥሰቶች በተደጋጋሚ ስንመለከትበት በታየው ጨዋታ በሁለቱም በኩል ተጨማሪ ጎሎች ሳይቆጠሩበት 1 – 1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ከመድን ጋር ያደረገው ጨዋታ በፎርፌ ተሸናፊ እንዲሆን በፌዴሬሽኑ የተወሰነበት ቅዱስ ጊዮርጊስም መሪነቱን ለመድን አስረክቧል።

ጎፋ ሜዳ 04:00 ላይ የጀመረው የሠላም እና አዳማ ከተማ ጨዋታ በአዳማ 5 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል። አዳማዎች የበላይነታቸውን ባሳዩበት በዚህ ጨዋታ በጠንካራ የፊት አጥቂዎቻቸው አማካኝነት ባስቆጠሩት አምስት ጎል አሸንፈው ወጥተዋል። በጨዋታው ፍራኦል ጫላ ሐት-ትሪክ ከመስራቱ ባሻገር የውድድሩ ከፍተኛ ጎል አስቆጣሪነትን በ12 ጎሎች መምራት ጀምሯል። ቀሪውን የአዳማ ሁለት ጎሎች ነቢል ኑሬ ነው ያስቆጠረው።

06:00 ላይ መከላከያን ከኢትዮጵያ መድን ባገናኘው ጨዋታ በኢትዮጵያ መድን 2-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። በየጨዋታው ጥንካሬውን በማሳየት እየተሻሻለ የሚገኘው መድኖች ወገኔ ገዛኸኝ ባስቆጠራት ጎል ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ብዙም ሳይቆይ ለኢትዮጵያ መድን ጌታነህ ካሳይ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሮ ወደ እረፍት አምርተዋል። በሁለተኛው አጋማሽ ምስጋናው መላኩ ከፍ/ቅ/ምት የተመለሰውን ኳስ ወደ ጎልነት ቀይሮ መከላከያን ከሽንፈት ያልታደገች ማስተዛዘኛ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታው በመድኖች 2 – 1 አሸናፊነት ተፈፅሟል።

ውጤቱን ተከትሎ ኢትዮጵያ መድን በስድስተኛ ሳምንት ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገው ጨዋታ የተጫዋች ተገቢነት ያስያዘው ክስ ውሳኔ አግኝቶ ሦስት ንፁህ ጎል እና ሦስት ነጥብ ማግኘቱን ተከትሎ ነጥቡን ወደ 18 ከፍ አድርጓል። በአንፃሩ ቅዱስ ጊዮርጊስ ላይ ነጥብ መቀነሱን ተከትሎ በ19 ነጥብ ውድድሩን በአንደኝነት እየመራ ይገኛል።

08:30 ጃንሜዳ ኢትዮጵያ ቡናን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያገናኘው ጨዋታ 23ኛ ደቂቃ ላይ በጣለው ከባድ ዝናብ ምክንያት ተቋርጧል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡