ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ደደቢት ከ ጅማ አባ ጅፋር

የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ባቀረበው ጥያቄ ምክንያት ተራዝሟል ተብሎ በድጋሚ በተያዘለት ጊዜ እንዲደረግ የተወሰነው ይህ ጨዋታ በዛሬው ዳሰሳችን እንዲህ ቃኝተነዋል።

በደሞዝ ምክንያት ልምምድ ካቋረጡ ከቀናት ቆይታ በኃላ ወደ ልምምድ የተመለሱት ደደቢቶች ወደዚህ ጨዋታ ዘግይተው እና የአንድ ቀን ልምምድ ብቻ ሰርተው እንደመቅረባቸው አሰልጣኝ ዳንኤል ፀሃዬ በሁኔታዎች ተገደው የሚመርጡት አጨዋወት ለመገመት ከባድ ቢሆንም ከባለፉት ጨዋታዎች በተሻለ ጥንቃቄ የተሞላው አጨዋወት ምርጫቸው ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከዚህ በተጨማሪ ባለፈው ሳምንት በቅጣት ያልተሰለፈው መድሃኔ ብርሃኔ ቅጣቱ ጨርሶ መመለሱ ለዳንኤል ፀሃዬ ጥሩ ዜና ሲሆን በሁለተኛው ዙር በጉዳት ምክንያት ቡድኑን በሚገባ ማገልገል ያልቻሉት አቤል እንዳለ እና ኩማ ደምሴም እንዲሁ መመለሳቸውም ለቡድኑ ሌላ ጥሩ ብስራት ሆኗል። በአንፃሩ ከመከላከያ ጋር በነበረው ጨዋታ በተመለከተው ቀይ ካርድ  ቅጣቱን ያልጨረሰው ጋናዊው ፉሴይኒ ኑሁ ከጨዋታው ውጪ ነው።

በሁለተኛው ዙር ከመጀመርያው ዙር በተሻለ በጥሩ የአሸናፊነት ስሜት የሚገኙት ጅማዎች ጥሩ ጉዟቸው በተከታታይ ሶስት ነጥቦች ለማጀብ በዚህ ጨዋታም ባለፉት ጨዋታዎች ውጤታማ ያደረጋቸውን በሁለት የአጥቂ ክፍል ተጫዋቾች  ኢላማ ያደረገ አጨዋወት ይከተላሉ ተብሎ ይጠበቃል። ከቅርፅ ለውጥ ባለፈ ሳምንት ተገማቹ አጨዋወታቸውን ለመቀየር በሚመስል መልኩ  መሃል ለመሀል ጥቃት ለመፈፀም በፈጣሪ አማካዮች የተዋቀረው የአማካይ ክፍል ምርጫቸው ያደረጉት አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ በዚህ የሜዳ ውጪ ጨዋታ  ታታሪነትን ወደ ተላበሱ የመሀል ክፍል ተጫዋቾቻቸው ፊታቸውን እንደሚያዞሩ ይጠበቃል። በጨዋታው ጅማዎች የአምበላቸው ኤልያስ አታሮ እና መስዑድ መሀመድን ግልጋሎት በጉዳት ሳቢያ የማያገኙ ሲሆን የአስቻለው ግርማ መሰለፍም አጠራጣሪ ነው። ከሁሉም በላይ ግን ጨዋታው እንደሚካሃድ ከተረጋገጠ በኋላ ተበታትኖ ወደ ስፍራው እያመራ የሚገኘው ቡድኑ እስካሁን ሙሉ ለሙሉ አለመግባቱ እና የመጨረሻ ልምምድም አለመስራቱ ነገሮችን እንዳያከብድበት ያሰገዋል።

የእርሰ በርስ ግንኙነት እና እውነታዎች

– በደደቢት ላይ ከፍተኛ የእርስ በርስ የበላይነት ያለው ጅማ አባ ጅፋር በሦስት ጨዋታዎች የ2-1 ፣ 3-0 እና 1-0 ድሎችን አሳክቷል።

– በትግራይ ስታድየም እስተሸንፏል። ጨዋታዎችን ያደረገው ደደቢት ሁለት ድል እና አንድ የአቻ ውጤት ሲያስመዘግብ በሌሎቹ ተሸንፏል።

– ጅማ አባ ጅፋር ከሜዳ ውጪ ካደረጋቸው አስር ጨዋታዎች ሦስቴ በድል ሁለት ጊዜ ደግሞ በአቻ ውጤት ሲመለስ በአምስት ጨዋታዎች ተሸንፏል።

ዳኛ

– እስካሁን አምስት ጨዋታዎችን የዳኘው ወልዴ ንዳው ይህን ጨዋታ እንዲመራ ተመድቧል። አርቢትሩ በሚያስገርም መልኩ በሁሉም ጨዋታዎች ላይ አምት አምስት የማስጠንቀቂያ ካርዶችን መዟል

ደደቢት (4-2-3-1) 

ሙሴ ዮሃንስ

ዳግማዊ አባይ – አንቶንዮ አቡዋላ – ሃይሉ ገብረየሱስ – ሄኖክ መርሹ

ያብስራ ተስፋዬ – ኤፍሬም ጌታቸው

መድሃኔ ብርሃኔ – አለምአንተ ካሳ – እንዳለ ከበደ

መድሃኔ ታደሰ

ጅማ አባጅፋር (4-4-2 ዳይመንድ) 

ዳንኤል አጄዬ

ዓወት ገ/ሚካኤል – መላኩ ወልዴ – አዳማ ሲሶኮ – ተስፋዬ መላኩ

አክሊሉ ዋለልኝ

ዲዲዬ ለብሪ – ይሁን እንዳሻው

ዋለልኝ ገብሬ

ኦኪኪ አፎላቢ – ማማዱ ሲዲቤ


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡