ሁለቱ ኢትዮጵያውያን ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ በሚደረገው ጨዋታ ይፋጠጣሉ

ሰላሳ አንደኛው ሳምንት የግብፅ ፕሪምየር ሊግ ኤልጎና እና ስሞሐን በስታደ አሌክሳንድሪያ ሲያገናኝ ሁለቱ ኢትዮጽያውያም ዑመድ ኡኩሪ እና ጋቶች ፓኖም ለወሳኙ ሶስት ነጥብ ዛሬ ማታ እርስ በርስ ይገናኛሉ።

በተከታታይ ጨዋታዎች የአሰልጣኙን ቀዳሚ ምርጫ መሆን የቻለው ዑመድ ኡክሪ በዚህ ጨዋታም የሆሰም ሐሰን ቀዳሚ ምርጫ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። ስሞሐዎች አስከፊ ስድስት ተከታታይ ሽንፈት አጋጥሟቸው ደረጃቸው በእጅጉ ካሽቆለቆለ በኃላ ሃራስ ኤልሆዳድ ፣ ዳክልይ እና ኤል ኢንታግ ኤል ሐርቢን በተከታታይ አሸንፈው እፎይታ ያገኙ ሲሆን ይህን ወሳኝ ጨዋታ ማሸነፍ ከወራጅ ቀጠናው ስለሚያርቃቸው ቀላል ግምት አይሰጣቸውም።

ከአስደናቂው የመጀመርያ ዓመት የሊጉ ቆይታቸው በኃላ ቀሰ መንሸራተት ያሳዩት እና ጋይሽን ካሸነፉበት የባለፈው ሳምንት ጨዋታ በፊት ላለፉት ስድስት ጨዋታዎች ሙሉ ሶስት ነጥብ ማግኘት ተስኗቸው የቆዩት የሐሚድ ሳዲቅ ኤል ጎናዎች እንደተጋጣምያቸው ስሞሐ ሁሉ የወራጅነት ስጋት ካንዣበበት ቀጠና ለመውጣት ከማሸነፍ ውጭ አማራጭ የላቸውም። ከጥቂት ጨዋታዎች በስተቀር ዓመቱን ሙሉ የአሰልጣኙን ቀዳሚ ተመራጭ መሆን የቻለው ጋቶች ፓኖም በዚህ ጨዋታም በቋሚነት ቡድኑን ያገለግላል ተብሎ ይጠበቃል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡