ከፍተኛ ሊግ ሐ | ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ ቢጥልም ተከታዩ በመሸነፉ ልዩነቱን አስፍቷል

የከፍተኛ ሊጉ ምድብ ሐ ጨዋታዎች እሁድ ተደርገው መሪው ሀዲያ ሆሳዕና ነጥብ የተጋራበት፤ ተከታዩ አርባምንጭ ከተማ የተሸነፈበት ውጤቶች ተመዝግበዋል።

የምድቡ መሪ ሀዲያ ሆሳዕና ቦረና ላይ ከነጌሌ ቦረና ጋር 1-1 አቻ ተለያይቷል። በ18ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት ያገኙት ቦረናዎች ምናሉ ተፈራ አስቆጥሮ ለረጅም ሳዓት መምራት ችለው ነበር። በ73ኛው ደቂቃ ላይ የቡድኑ አምበል የሆነው ትዕግስቱ አበራ የአቻነቱን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል። ሆሳዕና ምንም እንኳን አቻ ቢወጣም ተከታዩ አርባምንጭ በመሸነፉ ልዩነቱን በአንድ ከፍ በማድረግ ወደ ስድስት ማስፋት ችሏል።

ተከታዩ አርባምንጭ ከሜዳው ውጪ በቤንች ማጂ ቡና 2-0 ተሸንፎ ልዩነቱን የማጥበብ እድሉን አምክኗል። ሚዛን ላይ በተካሄደው በዚህ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ የታየበት ሲሆን አርባምንጮች ለግብ የቀረበ ሙከራ በአጥቂው ስንታየሁ አማካኝነት ማድረግ ቢችሉም በእለቱ ጥሩ ብቃት ላይ የነበረው ግብ ጠባቂው ሊሌሳ አማካኝነት ግብ ከመሆን ድነዋል። በቤንች ማጂ በኩል ጌታሁን ገላዬ የአርባምንጭ በረኛ ከግብ ክልል መውጣትን ተከትሎ የመታት ኳስ ከግቡ አናት ላይ ወጥታለች።

በሁለተኛው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው አጥቂው ልዩነት ፈጥሮ በመውጣት በቡድኑን አሸናፊ አድርጓል። ወንድማገኝ በ80ኛው ደቂቃ ከቅጣት ምት የተሻገረለትን ኳስ በግሩም አጨራረስ ከመረብ ሲያሳርፍ ከ5 ደቂቃ በኋላ በድጋሚ የራሱን ብቃት 2ኛ ጎል ማስቆጠር ችሏል።

ወራቤ ላይ ጅማ አባ ቡናን ያስተናገደው ስልጤ ወራቤ 2-0 አሸንፏል። በ25ኛው እና 50ኛው ደቂቃ ጢሞጢሞስ ቢራጋ ለወራቤ ጎሎችን በማስቆጠር ቡድኑን በድጋሚ ሶስተኛ ደረጃ እንዲይዝ አስችሎታል።

ቦንጋ ላይ ካፋ ቡና ነቀምት ከተማን 1-0 አሸንፏል። በ88ኛው ደቂቃ ላይ ኦኒ ኡጅሉ ነው ብቸኛዋን ጎል ያስቆጠረው። ሻሸመኔ ላይ ሻሸመኔ ከተማ ቢሾፍቱ አውቶሞቲቭን በተመሳሳይ 1-0 ሲያሸንፍ በ30ኛው ደቂቃ ላይ ዳንኤል ኃይሌ ብቸኛዋን ግብ አስቆጥሯል።

ቡታጅራ ላይ ቡታጅራ ከሺንሺቾ ያደረጉት ጨዋታ 2-2 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል። ለሺንሺቾ ተመስገን በጅሮንድ እና ብርሃኑ ኦርዴሎ ሲያስቆጥሩ ለቡታጅራ ሙፍሪድ እንድሪስ እና ክንዴ አብቹ አስቆጥረዋል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡