የአሰላ ኅብረት ከ20 ዓመት በታች ቡድን የመፍረስ አደጋ ተጋርጦበታል

በ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ ምድብ ለ ውስጥ እየተወዳደረ የሚገኘው አሰላ ኅብረት በበጀት ዕጥረት ሳቢያ ሕልውናውን ሊያጣ ተቃርቧል።

ዘንድሮ በአሰላ ኅብረት አምና ደግሞ በጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ ስም የምናውቀው የ20 ዓመት በታች ቡድን መነሻውን በኒያላ ፣ ሐረር ቢራ ፣ መብራት ኃይል ፣ ንግድ ባንክ እና ወልዲያ ተጫውቶ ባሳለፈው ከአሰልጣኝ ዐቢይ ወርቁ የላማሲያ ፕሮጀክት ያደረጋል። ሲጀመር ከ17 ዓመት በታች የነበረው ቡድኑ አሰላን በመወከል በ2009 አዳማ ላይ በተደረገው የኦሮሚያ ፕሮጀክቶች ምዘና ውድድር ላይ በሦስተኝነት ማጠናቀቁን ተከትሎ ተጫዋቾቹን ሳይበትን ወደ ሊግ ውድድር ለመግባት በወቅቱ በርካታ ጥረቶች አድርጓል። በመጨረሻም ከጭላሎ ፉድ ኮምፕሌክስ ባገኘው ድጋፍ አምና በኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪምየር ሊግ የድርጅቱን ስያሜ በመያዝ የመወዳደር ዕድል ማግኘት ችሏል። በውድድሩም በተደለደለበት ምድብ ሀ በ14 ጨዋታዎች 11 ነጥቦችን በመያዝ የመጨረሻ ደረጃን ይዞ ቢጨርስም አራት ተጫዋቾችን ለዕድሜ ዕርከኑ ብሔራዊ ቡድን ማስመረጥ ችሎ ነበር።

ሆኖም የዘንድሮው ሁለተኛው የውድድር ዓመቱ ላይ የተሻለ ልምድ ይዞ መልካም እንቅስቃሴ ያደርጋል ተብሎ ቢጠበቅም ለቡድኑ እና ለአሰልጣኙ ከባድ ጊዜ ሆኗል። ምክንያቱ ደግሞ ጭላሎ ፉድ ኬምፕሌክስ ቡድኑን ለከተማ አስተዳደሩ ማስረከቡን ተከትሎ ያገኝ የነበረውን ድጋፍ በማጣቱ እንደ ቡድን በሊጉ እየተወዳደረ ለመቀጠል ያማይችልበት ደረጃ ላይ በመድረሱ ነው። ክለቡን በአክሲዮን መልክ ለማቋቋም የተደረገው ጥረትም የከተማዋ አስተዳደር አክሲዮኑ ከአስር ሰዎች በላይ እንዳያካትት ፍቃድ ባለመስጠቱ ሳይሳካ ቀርቷል። ነገር ግን ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ የከተማዋ ነዋሪ የሆነው አቶ አሰፋ ጅፋር ባደረገው ጥረት አሰላ ኅብረት በሚል ስያሜ በውስን አቅም ወደ ዘንድሮው ውድድር ገብቷል። ሆኖም 14 ተጨዋቾችን ወደ ተለያዩ ክለቦች የለቀቀው ቡድኑ ባሰበው መንገድ ራሱን ማጠናከር ሳይችል ተሳትፎውን ቢቀጥልም በተለይም የመጀመሪያውን ዙር ከጨረሰ በኋላ የፋይናንስ አቅሙ እጅግ በመዳከሙ ሰፋፊ እና ተከታታይ ሽንፈቶችን እያስተናገደም ይገኛል። በበቂ ሁኔታ የምግብ እና ሌሎች ወጪዎችን መሸፈን አለመቻሉ ደግሞ በታዳጊዎቹ ሞራል ላይ ባደረሰው ጫና ውጤቱ ሊስተካከል አልቻለም።

የአካባቢው ታዳጊዎች በክለብ ደረጃ የመጫወት ህልማቸውን ለማሳካት መሰል ቡድኖች መሸጋገሪያ ይሆኗቸው ዘንድ የሚያስፈልጓቸው ቢሆንም ከአመታት በፊት እንደ ሙገር ሲሚንቶ ያለ ትልቅ ክለብ መቀመጫ በነበረችው አሰላ ከተማ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘው አሰላ ኅብረት የሚደግፈው አካል ማግኘት ባለመቻሉ ህልውናው አሁን ላይ ቀጣይነት ያለው አይመስልም። ይህ ሆኖ የታዳጊዎቹ ህልም መና ከመቅረቱ በፊት ከጎናቸው የሚቆም አካል እንደሚያስፈልጋቸው የሚናገረው አሰልጣኝ ዐቢይ ወርቁ ከዋና ክለቦች ጋር ሲነፃፀር በጥቂት በጀት መንቀሳቀስ በሚቻልበት የታዳጊዎች እግር ኳስ ላይ ከአቶ አሰፋ ጅፋር እና ጓደኞቹ የግል ጥረት በቀር አጋዥ አለማግኘቱ እንዳሳዘነው ገልፆ ነገሮች በዚሁ ከቀጠሉ ግን ቡድኑ የመበተን ዕጣ ሊያገኘው እንደሚችል ለድረ ገፃችን አስረድቷል።


© ሶከር ኢትዮጵያ

በድረ-ገጻችን ላይ የሚወጡ ጽሁፎች ምንጭ ካልተጠቀሱ በቀር የሶከር ኢትዮጵያ ናቸው፡፡ እባክዎ መረጃዎቻችንን በሚጠቀሙበት ወቅት ምንጭ መጥቀስዎን አይዘንጉ፡፡